አቶ ገብሩ አስራት ጦርነቱ እንዳይጀመር ጥረት አድርገው እንደነበር ገለጹ
“ራያ እና ወልቃይት ሰበቦች እንጅ የጦርነቱ ዋነኛ ምክንያቶች አይደሉም” ብለዋል አቶ ገብሩ
ፖለቲከኛው አቶ ገብሩ የጦርነቱ ጅማሬ የሠሜን ዕዝ ተጠቃ የተባለ ጊዜ “ነው ብዬ መደምደም አልችልም” ብለዋል
በፓርቲም ሆነ በግለሰብ ደረጃ በኢትዮጵያ ጦርነት እንዳይካሄድ ብዙ ጥረት አድርገው እንደነበር የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገብሩ አስራት ገለጹ፡፡
የቀድሞው የትግራይ ክልል ርዕሠ መስተዳድርና የአሁኑ የአረና እና የመድረክ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ገብሩ አስራት ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
አቶ ገብሩ ከአል ዐይን ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በኢትዮጵያ ጦርነት እንዳይካሄድ ጫና ሲያሳድሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ነገር በሰላማዊ ድርድርና ውይይት እንዲፈታ ቀደም ሲል ዲፕሎማቶችና መንግስት እንዲያውቁት ማድረጋቸውንም አቶ ገብሩ አስታውቀዋል፡፡ ለጦርነቱ መቀስቀስ ብዙ ምክንያቶችና ሰበቦች እንዳሉት የገለጹት አቶ ገብሩ፤ የተለያየ ፍላጎትና ጥቅም ያላቸው ሃይሎች ተሳትፈዋል ብለዋል፡፡
- ዓረና፤ በሀገራዊ ምክክሩ “ህወሃት እና ኦነግ ሸኔ ካልተሳተፉ ዋጋ የለውም” አለ
- “እኔ በአንድ ነገር ገለልተኛ አይደለሁም፤ ያ አንድ ነገር ምንድነው ካልከኝ ኢትዮጵያዊነት” - ፕ/ር መስፍን አርዓያ
ቀደም ሲል “በኢህአዴግ ውስጥ በፖለቲካ አግባብ ብዙ ትግል ነበር” ያሉት አቶ ገብሩ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ “በህወሃትና ስልጣን በያዘው ኦህደዴ ብልጽግና (ወሳኙ እሱ ስለሆነ) መካከል ከፍተኛ ፉክክር ተነስቶ ነበር”ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት አዲስ ስልጣን የያዙት “እነ ዶ/ር ዐቢይ ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ሲሞክሩ ህወሃት ደግሞ ከስልጣን የተገፉበት ሁኔታ ነበር መንገድ ነበር፤ ይህንን በሰከነ፣ በበሰለና በተደራጀ መንገድ ለመፍታት ሙከራ አልተደረገም”’ ያሉት አቶ ገብሩ ይህም ጦርነት ለመከሰቱ ትልቁ ምክንያት ነበር ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለጦርነቱ መነሻ ምክንያት እንደሆነ አቶ ገብሩ ያነሱት የኤርትራ መንግስት ሲሆን፤ እርሱም ይህንን ያደረገው በኢትዮ ኤርትራ ወቅት ባለው ቂም እና አካባቢውን ለመቆጣጠር ካለው ሕልም የተነሳ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አቶ ገብሩ፤ የኤርትራ መንግስት “ህወሃት መጥፋት አለበት” የሚል አቋም በማራመድ መግለጫዎችን ሲሰጥ እንደነበር አንስተው የጦርነቱ መነሻ የስልጣን ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ብዙዎቹ የተቀላቀሉት ተገፍተው እንደሆነ ያነሱት አቶ ገብሩ ፤ ጦርነቱ ከፖለቲካ ሽኩቻ አልፎ የእርስ በእርስ ጦርነት እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡
ጦርነቱን ማን ጀመረው?
አቶ ገብሩ አስራት ጦርነቱን ማን ጀመረው በሚለው ጉዳይ ላይ “ለጦርነቱ ሁሉም ተዘጋጅተው ነበር፤ ፖለቲካዊ ሽኩቻው ጥርዝ ላይ ደርሶ ነበር” ብለዋል፡፡ እርስ በእርስ የነበረው ሽኩቻ ወደ ጦርነት ሊያመራ እንደሚችል ይገመት ነበር የሚሉት አንጋፋው ፖለቲከኛ በሁሉም ተዋንያን ማለትም በመንግስትና በኤርትራ በኩል ዝግጅት ተደርጎ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ህወሃት አደጋ እንደተደቀነበትና አደጋ ያለውንም ጉዳይ በጦር ጭምር ለመከላከል ቀደም ብሎ ዝግጅት ማድረጉንም አቶ ገብሩ ጠቅሰዋል፡፡ የአረናው መስራች አቶ ገብሩ፤ የጦርነቱን መነሻ በተመለከተ የመጀመሪያውን ጥይት ማን ተኮሰው ሊባል እንደማይገባ አንስው አንደኛቸው ይጀመሩት ይችላል ከማለት ውጭ እከሌ ነው አላሉም፡፡
ህወሃት በአቶ ሴኩ ቱሬ በኩል በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን መግለጹን ተከትሎ ጦርነቱን እንደጀመረው ይገለጻል፡፡ አቶ ገብሩም ህወሃት “አስቀድሜ የመከላከል እርምጃ ወስጃለሁ”ማለቱን የገለጹ ሰሆን እንደ ኦፕሬሽን ሰሜን ዕዝ ከፍተኛው እንደነበር፤ ይሁንና የጦርነቱ ጅማሬ “ያኔ ነው ብዬ መደምደም አልችልም፤ ዝግጅቱ ነበረ ቀደም ሲልም ጨዋታው አልቋል የሚባል ነገር ነበር እኮ” በማለት መልሰዋል፡፡
ከ1993 ዓ.ም የሕወሃት ክፍፍል በኋላ ድርጅቱን ለቀው የወጡ አመራሮች ወደ ጦርነቱ መመለሳቸውን ተከትሎ እርስዎስ አልተጋበዙም ወይ የሚል ጥያቄም ለአቶ ገብሩ ቀርቦላቸዋል፡፡ “ከ2011ዓ.ም ጀምሮ መመከት አለብን ብለው ነበር፤ በጦርም እንመክታለን ብለው ነበር፤ በዚህ የመመከት ጉዳይ በጦርነቱ መጥተህ እርዳን ተሰለፍ የሚል ነገር መጥቶብኝ ነበር” ብለዋል፡፡ መልዕክቱ የመጣው ከአመራር በተላከ ሰው እንደሆነ ያነሱት ፖለቲከኛ አቶ ገብሩ፤ “እኔ ፖለቲካሊ እንመክታለን፤ አስቀድሞ ለጦር ዝግጅት ከሆነ እኔ ዝግጁ አይደለሁም ብያለሁ፤ ኢፍትሃዊ ጫና ከተጫነብን አይተን እንሳተፋለን አስቀድሞ መዘጋጀት ለፖለቲካ፣ ለዲፕሎማ፣ ለእርቅና ለሰላም መሆን አለበት እንጅ ለጦርነት አይደለም ብያለሁ” ብለዋል፡፡
ራያ እና ወልቃይት የጦርነቱ መነሻዎች ናቸው?
የራያ እና ወልቃይት እንዲሁም ሌሎች የማንነት ጥያቄዎች ሰበቦች እንጅ የጦርነቱ ዋነኛ ምክንያቶች እንዳልሆኑ አቶ ገብሩ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡ እንኳን በአንድ ሀገር ውስጥ በሌሎች ሀገራትም መሃል ድንበር ሊያዋጋ ይችላል በአብዛኛው በሰላም በህግ ይፈታል ብለዋል፡፡ ሕግንና ሕገ መንግስትን ተከትሎ መፍታት ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ድንበር በተለያዩ ወቅቶች በተለይ ከአጼ ምንሊክ በኋላ ሲቀያየር እንደነበር ገልጸው በዛው የትግራይም ቅርጽ ተቀያይሮ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በአንድ ወቅት የትግራይ ግዛት እስከ አለውሃ ጸለምትና አፋርን ጭምር ያካትት እንደነበርና በኋላ ደግሞ አላማጣና ኮረም ወደ አማራ ክልል ታጥፈው እንደነበር የቀድሞው የትግራ ክልል ርዕሠ መስተዳድር ገልጸዋል፡፡
“ከ1985ዓ.ም በኋላ የመጣው አከላለል መሬት የመውሰድ አከላለል አልነበረም” የሚሉት አቶ ገብሩ አስራት ፤ የአከላለል መርሁ በቋንቋና በብሔር እንደሆን ተወስኖ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ የ1985ዓ.ም አከላል ዘላቂ ላይሆን እንደሚችል ያነሱ ሲሆን፤ ሕዝቡ መክሮበት አያስፈልግም ካለ ሊቀይረው እንደሚችልና ሌላ አከላለልም ሊመጣ እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡
በአንድ ሀገር ያለው የወሰን አከላለል በየወቅቱ ሊቀያየር እንደሚችልና ቋሚ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ የድንበር ጉዳይ ይህ ሁሉ ሕዝብ ላለቀበት ጦርነት ሰበብ ይሆናል ብለው እንደማያስቡም አቶ ገብሩ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ አከላለልን በተመለከተ መለወጥ ካለበት የራያና ወልቃይት ብቻ በማንሳት ሳይሆን በአጠቃላይ መቀየር አለበት ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡
አቶ ገብሩ፤ ቤኒሻንጉል ክልል ከፊል ከጎጃም፤ ከፊል ከወለጋ ተወስዶ እንደተቋቋመ የገለጹ ሲሆን ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ በራህሌ እና አፍዴራ የሚባሉ አካባቢዎች በትግራይ ስር እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ አዲስ አከላለል ሲመጣ በሀብት ወይም በመሬት ስፋት ቢሆን ኖሮ አሁን በአፋር ስር ያሉት መልቀቅ ይገባ ነበር ወይ ሲሉ ጉዳዩን በጥያቄ መልሰዋል፡፡ ወደ ክፍለ ሀገር እንደመለስ ካልን እንደገና ነው ለውጥ መደረግ ያለበት ይላሉ፤
የትግራይ አማጺያን ከአፋር እና ከአማራ ይውጡ የሚሉ ጥያቄዎች እንዳሉ ያነሱት አቶ ገብሩ፤ የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ ክልል ይውጣ የሚል ጥያቄ ለምን አልተነሳም ብለዋል፡፡
የራያ እና ወልቃይት ጉዳይ በምን ይፈታ?
አቶ ገብሩ አስራት የራያ እና ወልቃይት ጉዳይ በሕግና በሕገ መንግስት እንደሚፈታ እምነት አላቸው፡፡ ሕገ መንግስቱ ላይ ብዙ ችግሮች እንዳሉ የሚቀርቡ ጥያቄዎአች እየተነሱ በመኖራቸው እርሱ እንደት ችግር ሊፈታ ይችላል የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ገብሩ፤ መንግስት እየተመራ ያለው በዚህ ሕገ መንግስት በመሆኑ መፍታት ይቻላል ብለዋል፡፡
ከሕግ ውጭ በጉልበት እንመልስ ከተባለ የማያባራ ጦርነት ሊከሰት እንደሚችልም አቶ ገብሩ የገለጹ ሲሆን ችግሮቹን ለመፍታት ግን በሰላም መነጋገር ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ይሁንና አሁን ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊሂቃኑ ያጦዙትና ሰከን ብሎ መነጋገርን ያላስቀደመ ነው ብለዋል አቶ ገብሩ፡፡
ሕገ መንግስቱ የጸደቀው ራያ እና ወልቃይት ወደ ትግራይ ከተካለሉ በኋላ መሆኑ ችግሩን በሕገ መንግስት ለመፍታት አይቻልም የሚል ጥያቄ ከተለያዩ አካላት ቢነሳም፣ አቶ ገብሩ ግን ሕገ መንግስቱ በኋላ ቢመጣም በፊት ቢመጣም የክልሎችን ቁጥር ስላስቀመጠ ችግሩን በሕግ መፍታት ይቻላል ብለዋል፡፡