“መንግስት አሁን እየተከተለ ያለው አካሄድ በ2010 ኢህአዴግን ወደ ቀውስ ያስገባው ነው”- አቶ ገብሩ አስራት
“ልክ እንደ ድሮው ህወሃት፣ አሁን ላይ ወሳኝ ቦታ የያዘው ኦህዴድ /ኦሮሚያ ብልጽግና ነው” ብለዋል
“ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የሚያመጣ ንግግር ካልተደረገ ከዚህ በኋላ እንደሀገር ልናስብ አንችልም”
ብልጽግና አንድ የተዋሃደ ፓርቲ እንደሆነ ቢገለጽም፤ ፓርቲው ግን “ልክ እንደ ኢህአዴግ ነው” ሲሉ የትግራይ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገብሩ አስራት ገለጹ።
ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ገብሩ፤ በኢህአዴግ ጊዜ ህወሃት ወሳኝ ቦታ እንደያዘ ገልጸው አሁን ወሳኝ የሥልጣንና የውሳኔ ቦታ የያዘው “ኦህዴድ ወይም የኦሮሞ ብልጽግና ነው” ብለዋል።
በኢህአዴግ ጊዜ አራቱ ክልሎች ባሏው ፓርቲዎች ኢህአዴግን ቢያቋቋሙም ዋናው ስልጣን ተይዞ የነበረው ግን በህወሃት እንደነበር ተናግረዋል።
እርሳቸው የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እያሉ ህወሃት ከሌሎች በበለጠ የመወሰን ስልጣን እንደነበረው አንስተው፤ የአሁኑ ብልጽግና ፓርቲ የኢህአዴግን ቦታ ተክቶ እንደያዘ ነው የተናገሩት።
አቶ ገብሩ፤ ኢህአዴግ ፈርሶ ብልጽግና ፓርቲ ቢመሰረትም አሁንም “ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ደኢህዴን፣ እንዳሉ ናቸው” ብለዋል።
“እንደድሮው ህወሃት ሁሉ አሁን ላይ ወሳኝ ቦታ የያዘው ኦህዴድ ወይም የኦሮሚያ ብልጽግና እንደሆነም ነው” ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩት።
አሁን ብልጽግና ፓርቲ ውስጥ አፋር ፣ ሱማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሀረሪና ጋምቤላ ቢካተቱም ውሳኔዎችን የሚወስነው ማነው? የውሳኔ ሃይል በማን እጅ ነው ያለው? የሚለውን ነገር ማየት አስፈላጊ እንደሆነም ነው አቶ ገብሩ የጠቀሱት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ የተመለሰ የሕዝብ ጥያቄ እንደሌለ የተናገሩት አቶ ገብሩ አስራት “እኔ ዐቢይን አይደለም እንደ ግለሰብ እያየሁ ያለሁት፤ በዚህም ጠቅላላ ተቋሙ የድሮው ነው” ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በቅርቡ ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ቀደም ሲል “ሁለተኛ የነበረው ብአዴን አሁን ተገፍቷል” ያሉት ፖለቲከኛው፤ “የኦሮሞ ብልጽግና የሚባለው ኦህደዴድ የነበረ፤ አማራ ብልጽግና የተባለው ደግሞ ብአዴን የነበረ ነው” ብለዋል።
አጠቃላይ የብልጽግና መዋቅር ሲታይ የኢህአዴግ እንደሆነ ያነሱ ሲሆን ነጻነትንና ልማት ጨምሮ አሁን ላይ ሌሎችን የማዳመጥና የማሳተፍ ጉዳይ ከበፊቱ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ አንስተዋል።
አቶ ገብሩ፤ አሁን ያለው የዶ/ር ዐቢይ መንግስት “የኢህአዴግ ቅጥያ ነው” ያሉ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሁን እየተከተሉት ያለ አካሄድ በ2010 ዓ.ም ኢህአዴግን ወደ ቀውስ የከተተው እንደሆነም ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ሕዝቡ የነጻነት፤ በነጻነት የመንቀሳቀስና የመናገር፤ የልማት፣ የሙስና ይወገድልን ጥያቄ፤ ቢያነሳም በእርሳቸው አረዳድ ግን እስካሁን የተመለሰ ጥያቄ እንደሌለ እንዳውም አንዳንዶቹ እንደባሰባቸው ነው ያነሱት።
አሁን በሀገሪቱ ያለው ሙስና እና ዝርፊያ በኢህአዴግ ጊዜ ከነበረውም የባሰ እንደሆነ የገለጹት አቶ ገብሩ “አሁን ያለው ያለው እበላ ባይ ካድሬ ነው” ነው ብለዋል።
አሁን ባለው ሁኔታ በሀገሪቱ “ከፍተኛ” አፈና እንዳለ የሚያመለክቱ ጉዳዮች መኖራቸውንም ነው ፖለቲከኛው አቶ ገብሩ የሚናገሩት።
የመንግስትና የፓርቲ መገናኛ ብዙኃን የተለየ ሃሳብ ያለውን ግለሰብ እንደማያቀርቡ እራሳቸው ምስክር እንደሆነ የሚነሱት አቶ ገብሩ፤ ይህ በኢህአዴግ ጊዜም የነበረ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ኢህአዴግ መሪ ፓርቲ በሆነ ጊዜ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ይታሰሩ እንደነበር አንስተው ይህ ድርጊት አሁንም እንዳለ ተናግረዋል።
ድርድር
ኢህአዴግ መሪ ፓርቲ በነበረበት ወቅት ከተለያዩ አካላት ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ እንዳልሆነው ሁሉ አሁን ብልጽግና ተመሳሳይ አቋም ማራመዱን አቶ ገብሩ ተናግረዋል። ከሰሞኑ ድርድር ይኖራል የሚሉ ዜናዎች መውጣታቸውን ተከትሎ አቶ ገብሩ ጉዳዩን “አሁን ይደረጋል የተባለው እኮ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ነው፣ ድርድሩ በትክክል ከጦርነቱ በፊት ቢሆን ኖሮ ብዙ ነገር ያድን ነበር ብለዋል።
ይሄ ሁሉ ከደረሰ በኋላ ድርድር ይደረጋል የተባለው የስልት ጉዳይ እንጅ እውነት የመርህና ኢትዮጵያን ወደሚፈለገው አቅጣጫ መለወጥ የሚያስችል እንደማይመስላቸው ተናግረዋል።
ፖለቲከኛው፤ አሁን ያለውን ሁኔታ መለወጥ የሚቻለው፤ ጦርነቱ ቆሞ በጦርነቱ የሚሳተፉት ሁሉም ተሳታፊ መሆን ሲችሉ እንደሆነ ገልጸው፤ ይህ ሁኔታ ለውጥ፣ ሰላምና ዕድገት ሊያመጣ እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ምንም እንኳን ህወሃትንና ብልጽግናን እንደ ፓርቲዎች ባይደግፏቸውም ድርድር ካደረጉና ወደሰላም ይህም ወደ ሰላም ካመጣቸው ሃሳቡን እንደሚደግፉ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል።
“የትግራይ ሕዝብ በታላቅ ችግር ውስጥ ነው ያለው” የሚሉት አቶ ገብሩ ሌላ ቦታም ስራ አጥነት እና ኑሮ ውድነት እንዲቀረፍ ፤ ሰላም እንዲመጣ የሚፈልጉ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ከማንኛውም ጊዜ በላይ አሁን ሰላም እንደሚያስፈልጋትና ኢትዮጵያ አሁን ሰላም የምትፈልገው አሜሪካውያን ወይም ምዕራባውያን ስላሉ አይደለም ብለዋል።
ጦርነት ሳይቆም ስለፖለቲካ ማውራት አስቸጋሪና የማይቻል ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ የከፋ ነገር እንዳይመጣ ፍርሃት እንዳላቸው አቶ ገብሩ ገልጸዋል።
ሀገሪቱ አሁን ያለችበትን ችግር ለመፍታት አሳታፊ፣ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትናና ዴሞክራሲ የሚያመጣ ንግግር መደረግ እንዳለበት ይህ ካልተደረገ ግን ከዚህ በኋላ እንደሀገር ልናስብ አንችልም ብለዋል።