በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት እስካሁን ወደ ቀድሞ ስራቸው ያልተመለሱ ፋብሪካዎች ቀጣይ እጣ ፈንታ ምንድን ነው?
ፋብሪካዎቹ ወደ ምርት ካለመመለሳቸው በላይ ባንኮች የወሰዳችሁትን ብድር ክፈሉ እያሉ እያስጨነቁን ነው ብለዋል
መንግስት በበኩሉ በጸጥታ ችግር ምክንያት ስራ ካቆሙ ኢንዱስትሪዎች መካከል 625ቱ ዳግም ማምረት ጀምረዋል ብሏል
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት እስካሁን ወደ ቀድሞ ስራቸው ያልተመለሱ ፋብሪካዎች ቀጣይ እጣ ፈንታ ምንድን ነው?
ከአራት ዓመት በፊት የትግራይ ሀይሎች መቀሌ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ ለሁለት ዓመት የዘለቀ ጦርነት መካሄዱ ይታወሳል፡፡
ይህ ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ በተካሄደ ድርድር የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ቆሟል፡፡
ስምምነቱን ተከትሎ በጦርነቱ ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩ ፋብሪካዎችን ዳግም ስራ ለማስጀመር የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
አል ዐይን አማርኛ በተለይም በትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩ ፋብሪካዎች ምን ላይ እንዳሉ ጠይቋል፡፡
ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፊት በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ የተለያዩ ግንባታዎች ግብዓትን ከሚያቀርቡ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የሆነው ሰማያታ ዕምነበረድ ፋብሪካ አንዱ ነው፡፡
በውቅሮ ከተማ የሚገኘው ይህ ፋብሪካ በጦርነቱ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ከወደሙ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ ሲሆን ፋብሪካው እስካሁን ወደ ስራ እንዳልተመለሰ የፋብሪከው የፋይናንስ ሀላፊ ሐዱሽ ሐይሉ ነግረውናል፡፡
እንደ ሀላፊው ገለጻ ፋብሪካው በሁለት ኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶች በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የተቋቋመ ሲሆን 200 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ገቢ በማስገኘት ላይ እያለ የወጣበትን ወጪ ሳይመልስ በተቋቋመ በአምስት ዓመቱ ወድሟል፡፡
600 ሰራተኞች ነበሩት የተባለው ይህ ፋብሪካ ከህዳር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ስራ አቁሟል የሚሉት ሀላፊው ቅንጡ ህንጻዎችን የሚገነቡ እና በኢትዮጵያ ቁጥር አንድ የሚባሉ ስራ ተቋራጮች ዋነኛ ደንበኞቻቸው እንደነበሩም አክሏል፡፡
ፋብሪካውን ዳግም ስራ ለማስጀመር ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ሐዱሽ በትንሽ አቅም ስራ ለመጀመር የተለያዩ ጥረቶችን እያደረግን ቢሆንም ባንኮች ከዚህ በፊት የተበደርነውን ብድር እንዲከፍሉ እየወተወቷቸው መሆኑ ትልቅ እክል ሆኖብናል ብለዋል፡፡
የፋብሪካው አምስት ሰራተኞች በጦርነቱ መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን ሌሎች ሰራተኞች የት እንደሆኑ እንደማይታወቅ፣ ለስልጠና ብዙ ወጪ የወጣባቸው ልዩ ባለሙያዎችም የት እንዳሉ እንደማያውቁም ሀላፊው ጠቅሰዋል፡፡
ሌላኛው በጦርነቱ ስራ አቁሞ ከነበሩ ፋብሪካዎች ውስጥ አንዱ የነበረው አልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሲሆን ከስድስት ወር በፊት ዳግም ስራ መጀመሩ ተገልጿል፡፡
የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ተክለማርያም ተስፉ ለአል ዐይን እንዳሉት ፋብሪካው ከጦርነቱ በፊት ከስድስት ሺህ በላይ ሰራተኞች እንደነበሩት እና አሁን ላይ በደረሰበት ውድመት ምክንያት በሁለት ሺህ ሰራተኞች ዳግም ስራ ጀምሯል ብለዋል፡፡
በአድዋ ከተማ የሚገኘው ይህ ፋብሪካ ስራ የጀመረው በ20 በመቶ አቅሙ ነው የሚሉት አቶ ተክለማርያም ወደ ቀድሞ ስራው እንዲመለስ የብድር እና የውጭ ምንዛሬ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡
በጦርነቱ ወቅት ፋብሪካው ስራ ባቆመበት ወቅት ለሰራተኞቹ ያልተከፈለ የ20 ወራት ውዝፍ ደመወዝ በድምሩ 420 ሚሊዮን ብር እዳ እንዳለበትም ሀላፊው ጠቅሰዋል፡፡
አቶ ተክለማርያም “ፋብሪካው ዳግም ወደ ስራ መግባቱን ተከትሎ የ36 ወራት ውዝፍ ደመወዝ 570 ሚሊዮን ብር ለሰራተኞች ተከፍሏል፡፡ ይሁንና ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ባለመመለሳችን ምክንያት በሙሉ አቅም ማምረት፣ መሸጥ ባለመቻላችን እና ገቢ በማጣታችን ያለብንን የባንክ ብድር ካለመክፈላችን በተጨማሪ የተጠራቀመ የሰራተኞች ውዝፍ ጡረታ አልከፈልንም፡፡ ከዚህ በፊት የተበደርናቸውን ብድሮች መክፈል ስላልቻልን ባንኮችን እና ጡረታ ተቋማትን እፎይታ እንዲሰጠን እየጠየቅን ነው“ ብለዋል፡፡
ሀላፊው አክለውም “ከጦርነቱ በፊት የነበሩ የሀገር ውስጥ ደንበኞቻችንን አጥተናል፡፡ ለአብነትም መንግስት የህክምና አልባሳት፣ የተማሪዎች ዩኒፎርም እና ሌሎች ምርቶችን ይገዛን ነበር አሁን ወደ ቀድሞ ምርት እየተመለስን ቢሆንም የገበያ ትስስር ድጋፍ ያስፈልገናል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በ400 ሚሊዮን ብር እንደተቋቋመ የተገለጸው እና በጦርነቱ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ወድሞ እስካሁን ወደ ስራ ካልተመለሱ ፋብሪካዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ደግሞ ሼባ ሌዘር ኢንዱስትሪ ነው፡፡
የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ እድል ገብረእግዚያብሔር እንደነገሩን ፋብሪካው በቀን ከ6 ሺህ በላይ የፍየል፣ በግ እና በሬ ቆዳዎችን ያለማ ነበር፡፡
ፋብሪካው ከ1 ሺህ በላይ ሰራተኞች ነበሩት የሚሉት ስራ አስኪያጁ ምርቶቹን አውሮፓ፣ አሜሪካ እና እስያ በመላክ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከሚያስገኙ ተቋማት መካከል አንዱ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡
የራሱ የቆሻሻ ማጣሪያ ቴክኖሎጂም ነበረው የተባለው ይህ ፋብሪካ ወደ ቀድሞ ስራው መመለስ ባለመቻሉ ፋብሪካው ከሚያጣው ጥቅም ባለፈ በሰራተኞች እና በሀገር ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ እንደሆነም አቶ እድል ተናግረዋል፡፡
አቶ እድል አክለውም ፋብሪካው ሙሉ ለሙሉ ስራ ካቆመ አራት ዓመት እንደሆነው፣ ጦርነቱ ብዙ ወጪ የወጣባቸው ማሽኖችን እና ባለሙያዎችን እንዳሳጣቸውም ጠቅሰዋል፡፡
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት አመራሮች እየመጡ ጎብኝተውናል የሚሉት ስራ አስኪያጁ ነገር ግን እስካሁን ዳግም ስራ ለማስጀመር የተደረገ ጥረት አላየንም ብለዋል፡፡
ፋብሪካው ለኢትዮጵያ አዲስ ቴክኖሎጂ በሆኑ ማሽኖች የተደራጀ እንደነበር የሚናገሩት አቶ እድል በአጠቃላይ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ንብረት ውድመት ደርሶበታልም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የትግራይ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ገብረመድህን ወልደማርያም በበኩላቸው በጦርነቱ ምክንያት በክልሉ ፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ሰራተኞች ለከፋ ጉዳት ተዳርገዋል ብለዋል፡፡
ከጦርነቱ በፊት በክልሉ ውስጥ በ55 የሰራተኞች ማህበራት ስር ተደራጅተው የነበሩ 70 ሺህ ሰራተኞች ነበሩ የሚሉት ሀላፊው አሁን ላይ ፋብሪካዎች ወደ ቀድሞ ማምረት ስራ ባለመግባታቸው የሰራተኞች ማህበራት ቁጥር ወደ 39 እንዲሁም የሰራተኞች ብዛት ደግሞ ከ15 ሺህ በታች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተለይም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን ቀጥረው ሲሰሩ ከነበሩ ፋብሪካዎች መካከል ዲዲኤል ኢትዮጵያ፣ ቬሌሲቲ፣ ሼባ ሌዘር እና በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ አምስት ፋብሪካዎች አሁንም ዳግም ወደ ስራ ባለመመለሳቸው ሰራተኞች ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ሀላፊው ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ እንዳሉት ትግራይ ክልልን ጨምሮ በጸጥታ ችግር ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ምርት እንዲገቡ እየሰራን ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥም ስራ ሙሉ ለሙሉ እና በከፊል አቁመው ከነበሩት ውስጥ 625 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲመለሱ አድርገናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው አሁንም ሙሉ ለሙሉ እና በከፊል ስራ አቁመው ያሉ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ማምረት ለማስገባት ከፋይናንስ ተቋማት እና ሌሎች ውሳኔዎችን ከሚያሳልፉ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራን ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
እንዲሁም ወደ ዳግም ምርት የገቡ ፋብሪካዎች የገበያ ትስስር በየጊዜው እየተፈጠረላቸው ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ለቀሪዎቹም በቀጣይ ተጨማሪ የገበያ ተስስሮችን እንዲያገኙ ይደረጋልም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩ ፋብሪካዎች ለስራቸው ተበድረዋቸው የነበሩ ብድሮች የመክፈያ ጊዜን ለአንድ ዓመት ከግማሽ አራዝሞ ነበር፡፡
ባንኩ ለጦርነቱ መቆም ምክንያት ከሆነው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኋላ የሰጠው የብድር መክፈያ ማራዘሚያ ጊዜ ከሁለት ወር በፊት የተጠናቀቀ ሲሆን ይህን የእፎይታ ጊዜ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ማራዘሙን አስታውቋል፡፡