“ከፍተኛ የኦክስጂን እጥረት አጋጥሞናል”- ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል
በግጭቱ የተለያዩ ጉዳት ያጋጠማቸውን በርካታ ታካሚዎች በማከም ላይ መሆናቸውንም የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ገልጸዋል

ሆስፒታሉ በኤሌክትሪክ አገልግሎቶች መቆራረጥ ምክንያት ሙሉ የራዲዮሎጂ ህክምና ግልጋሎቶችን ለመስጠት አለመቻሉንም ነው ያስታወቀው
በትግራይ ክልል የሚገኘው ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ታካሚዎች በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ክብሮም ገ/ስላሴ ገለጹ፡፡
በትግራይ የነበሩ የህክምና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በግጭቱ ምክንያት ስለወደሙና ስለተዘረፉ አሁን ሆስፒታሉ ከአቅም በላይ ተገልጋዮች ለማስተናገድ መገደዱንም ነው ዶ/ር ክብሮም እንደምክንያትነት ያስቀመጡት፡፡
ሜዲካል ዳይሬክተሩ ዶ/ር ክብሮም ለአል-ዐይን አማርኛ እንደገለጹት ግጭቱን ተከትሎ የመጀመርያዎቹ ወራት በተለይም ህዳር፣ታህሳስ እና ጥር ከባድ ጊዜያት ነበሩ፡፡ ምንም አይነት የመድሃኒት፣ ትራንስፖርት፣ የባንክ፣ ኤሌክትሪክ እና ኮምዩኒኬሽን አቅርቦትም አልነበረም፡፡
በግጭቱ ምክንያት ቀደም ሲል በሆስፒታሉ ህክምና ይከታተሉ የነበሩ ከተለያዩ አካባቢዎች ማለትም ትግራይን ጨምሮ ከአፋርና አማራ ክልል የሚመጡ የደም ግፊት፣ ስኳር እና ካንሰር ታካሚዎች አገልገሎት ለማቋረጥ ተገደው ነበር ያሉት ዶ/ር ክብሮም፤ አሁን ላይ በተወሰነ መልኩ ለውጥ መኖሩን በማከል፡፡
እንደ ዶ/ር ክብሮም ከሆነ አሁን በዓይደር የሚገኙ ታካሚዎች በግጭቱ ምክንያት “በጥይት ተመተው የቆሰሉ፣ ቦምብና ፈንጅ የረገጡ፣ በመድፍ በተመቱ አካባቢዎች የተጎዱ ከ3 ዓመት እስከ አዛውንት የእድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው”፡፡
ሌላው ሆስፒታሉ እያስተናገደ የሚገኘው መንገድ መከፈቱን ተከትሎ የመጡ በርካታ ቁጥር ያላቸው “የተደፈሩ ሴት እህቶቻችን ነው” የሚሉት ሜዲካል ዳይሬክትሩ ዶ/ር ክብሮም፤ የደረሰባቸው የሞራል ስብራት ለመጠገን የስነ-ልቦና እና የህግ ምክር አገልግሎት እየተሰጣቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በርሃብ የተጎዱ ህፃናትን ጭምር እያስተናገዱ እንደሆነም ነው ሜዲካል ዳይሬክተሩ የገለፁት፤ ህጻናቱ ምግብ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን በማከል፡፡
ሜዲካል ዳይሬክተሩ የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎች በከፍተኛ መስዋዕትነት እያገለገሉ ይገኛሉም ብለዋል፡፡
ባለሙያዎቹ “ለሶስትና አራት ቀናት ካለ ምንም እረፍት ቀዶ ጥገና የሚሰሩ፣ የሰዓት እላፊ አዋጅ በታወጀበት ህይታቸውን አደጋ ላይ ጥለው የሚሰሩ እና በሆስፒታሉ ዙሪያ ተኩሶች እየተሰሙ በነበሩበት ወቅት ጭምር ያን ሁሉ ተቋቁመው ካለ ምንም ተጨማሪ ክፍያ ያለፉትን 6 ወራት ሲሰሩ የነበሩ ናቸው” ሲሉም ነው ለሆስፒታሉ ባለሙያዎች ያላቸውን አድናቆትና ክብር የገለፁት፡፡
የህክምና ቁሳቁሶችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ እና ከጤና ሚኒስቴር የሚቀርቡ ቁሳቁሶች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡
መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር ከበድ ያሉ ከውጭ የሚመጡ መድሃኒቶች እንዳሉ የሚናገሩት ዶ/ር ክብሮም እነዚህም ከለጋሽ ድርጅቶች እና ከክልሉ ተወላጆች ጋር ግንኙነት በመፍጠር እየተገዙ የሚቀርቡበት ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ከፍተኛ የኦክስጂን እጥረት እንዳለ ነው የተናገሩት፡፡ እጥረቱን “ዜሮ በሚባል ደረጃ ነው” ሲሉም ነው ያስቀመጡት፡፡
ሆስፒታሉ ቀደም ሲል የራሱ ኦክስጂን ያመርት ነበር፡፡ ሆኖም ባጋጠመው የመለዋወጫ ቁሳቁሶች (Spare part) እጥረት ምክንያት ቆሟል እንደ ዶ/ር ክብሮም ገለጻ፡፡
እጥረቱን ለማቅለል በማሰብ በቬሎሲቲ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ኦክስጂን ለማምረት የተደረገው ጥረት ፋብሪካው በግጭቱ በመውደሙና በመዘረፉ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ከውጭ የመጡ ኦክስጂኑን የማምረቻ መለዋወጫዎች ጉምሩክ ላይ የቆዩም ሲሆን መንግስት እንዲለቀቁ ማድረጉንና ቶሎ ይደርሳሉ ብለን እንጠብቃለን ብለዋል፡፡ ችግሩ አሳሳቢና አስቸኳይ መፍትሄን የሚሻ ነው የሚሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ ለጊዜው ከደሴ በማስመጣት ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኤሌክትሪክ ኃይል የአቅርቦት ችግሮች ምክንያት ልክ እንደ ኦክሲጅኑ ሁሉ የራዲዮሎጂ ህክምና ግልጋሎቶች መቋረጣቸውንም ነው ዶ/ር ክብሮም የገለጹት፡፡ ከራጅ ውጭ የአልትራ ሳውንድ፣ የሲቲ ስካንም ሆነ የኤም.አር.አይ አገልግሎቶች የሉምም ብለዋል፡፡
በትግራይ እስካሁን ከ40 ሺ ለሚልቁ ሰዎች የኮሮና ክትባቶችን ለመስጠት ተችሏል ስለመባሉ አል ዐይን አማርኛ ከሰሞኑ መዘገቡ ይታወሳል፡፡