የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኮምቦልቻ መጋዘን ተዘረፈ
በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ 279 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ድርጅቱ ገልጿል
ድርጅቱ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ በኮምቦልቻ እና ደሴ አካባቢ ላሉ ተፈናቃዮች ድጋፍ ማድረግ እቅድ ነበረኝ ብሏል
የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) የኮምቦልቻ መጋዘኑ መዘረፉን አስታወቀ፡፡
በአማራ ክልል ኮምቦልቻ ከተማ በበሚገኙት መጋዘኖች እንድገለገል ከሳምንት በፊት ፈቃድ አግኝቼ ነበር ያለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም በመጋዘኖቹ ተከማችተው የነበሩ ምግብን ጨምሮ ሌሎች ሰብዓዊ እርዳታዎች መዘረፋቸውን ቃል አቀባዩ ቶምሰን ፊሪ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ቃል አቀባዩ በመግለጫው እንዳሉት የዓለም ምግብ ድርጅት ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል ኮምቦልቻ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያቀርብ ፍቃድ አግኝቶ ነበር፡፡
ሆኖም አሁን ያሉ የቅድመ ግምገማ መረጃዎች መጋዘኑ በከፍተኛ ሁኔታ መዘረፉንና የዕቃ ማከማቻ ክፍሎቹ መጎዳታቸውን አመልክተዋል እንደ ቶምሰን ፊሪ ገለጻ፡፡
ይህ ለብዙዎች ለማድረስ ታስቦ የነበረውን የሰብዓዊ እርዳታ መጠን ዝቅ እንደሚያደርገውና ጥቂቶችን ብቻ ለመደገፍ እንደሚያስገድድ ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት በኮምቦልቻ እና ደሴ አካባቢ ላሉ ተፈናቃዮች ድጋፍ የማድረግ እቅድ እንደነበረው የተናገሩት ቃል አቀባዩ 450 ሺህ ተፈናቃዮችን ለመርዳት በሂደት ላይ እንደነበሩም አክለዋል፡፡
ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ለተፈናቃዮች የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ የሚያስችሉ ስራዎችን እንዲያከናውኑም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ቃል አቀባዩ መጋዘኑ በማን እንደተዘረፈና ጉዳት እንደደረሰበት የገለጹት ነገር የለም፡፡ ደሴ እና ኮምቦልቻን ጨምሮ ሌሎች አጎራባች የአማራ ክልል አካባቢዎች በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት ቁጥጥር ስር መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ፕሮግራሙ እስካሁን ለ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን የተናገሩት ፊሪ ከዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ያህሉ በትግራይ ቀሪዎቹ ደግሞ በአማራ እና አፋር ክልሎች ላሉ ዜጎች የተደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ድርጅቱ በሶስቱ ክልሎች ለሚገኙ ለ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ በሂደት ላይ እንደሚገኝም ነው ያስታወቁት፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆኑን ያሳወቀው የዓለም ምግብ ፕሮግራም በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥም ተጎጂዎችን ለመርዳት 279 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገውም አክሏል፡፡
በአጠቃላይ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ጨምሮ በአገሪቱ ሌሎች አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች እና የአየር ንብረት መዛባት ምክንያቶች ለተጎዱ 12 ሚሊዮን ገደማ ዜጎች በቀጣዮቹ ስድስት ወራት የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ 546 ሚሊዮን ዶላር የበጀት ጉድለት እንዳለበትም ፕሮግራሙ ገልጿል፡፡