የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአፋር እና አማራ ክልሎች የመጀመርያ ዙር የምግብ እርዳታ ማድረሱን አስታወቀ
ደብሊው ኤፍ ፒ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ለመርዳት 426 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገውም አስታውቋል
ለትግራይ ክልል የሚደረገው እርዳታ “በተለያዩ እንቅፋቶች ምክንያት ወደ ኋላ ቀርቷል”ም ብሏል ፕሮግራሙ
የዓለም ምግብ ፕሮግራም(ደብሊው ኤፍ ፒ) በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ በአፋር እና አማራ ክልሎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች፤ የመጀመርያ ዙር የምግብ እርዳታ ማዳረሱን አስታወቀ፡፡
ደብሊው ኤፍ ፒ “በግጭቱ ምክንያት እርዳታዎችን ማዳረስ ያልተቻለባቸው ቦታዎች ቢኖሩም 2 ሺ 200 ሜትሪክ ቶን የሚገመት የምግብ እርዳታ ወደ ዋግኸምራ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች ለማዳረስ ተችሏል”ብሏል፡፡
በመጀመሪያው ዙር የእርዳታ ስርጭት 210 ሺ ሰዎች ለመርዳት እንደተቻለም ድርጅቱ ገልጿል ፡፡
በአፋር ክልል 80ሺ ሰዎች እርዳታ አግንኝተዋል ያለው ደብሊው ኤፍ ፒ፤ ካለው የችግሩ መጠን አንጻር በቀጣይ ዙር የሚረዱ ዜጎች ቁጥር ወደ 500 ሺ ሊያሻቅብ እንደሚችልም አስታውቋል፡፡
እንደ ፈረንጆቹ ከነሃሴ 15 ወዲህ በአማራ እና አፋር ክልሎች ለሚገኙ 300 ሺ ተፈናቃዮች የሰብዓዊ እርዳታ መዳረሱንም ነው የገለጸው፡፡
በአማራ ክልል አራት ሚሊዬን ዜጎች ችግር ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ
ለትግራይ ክልል የሚደረገው እርዳታ “በተለያዩ እንቅፋቶች፤ የሰብዓዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች እንደፈለጉ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ምክንያት ወደ ኋላ ቀርቷል”ም ብሏል ፕሮግራሙ።
ከግንቦት 27 ወዲህ ከሰሜን ምዕራብ እና ደቡብ ትግራይ ተፈናቅለው በትግራይ ክልል ለሚገኙ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች እርዳታ ማዳረሱንም ገልጿል፡፡
“እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 200 ሺ ህጻናት እንዲሁም እድሜያቸው ከ39 እስከ 71 የሆኑ ነፍሰጡር እና አጥቢ እናቶች” የተመጣጠነ የምግብ እርዳታን ካገኙ የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸውም ብሏል፡፡
የፕሮግራሙ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሚካኤል ዱንፎርድ “ሪፖርቶች እንደሚያመክቱት ከሆነ ፤ባለው ሁኔታ በርካታ ቤተሰቦች ከቤታቸው እየሸሹ በመሆናቸው በሶስቱም ክልሎች ያለው የምግብ እጥረት ሁኔታ እየጨመረ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ እስካሁን በአማራ እና አፋር ክልል ብቻ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች ለረሃብ ሊጋለጡ በሚችሉበት ደረጃ ላይ እየደረሱ መሆናቸው እንዲሁም 840 ሺ (700 ሺ በአማራ እና 140 ሺ በአፋር) የሚሆኑ መፈናቀላቸውንም ፕሮግራሙ መንግስትን ዋቢ በማድረግ ያወጣው መረጃ ይጠቁማል፡፡
በአፋር ክልል ህወሓት በፈጸመው ጥቃት 107 ህጻናትን ጨምሮ 240 ተፋናቃዮች መግደሉን የክልሉ መንግስት አስታወቀ
እንደ ደርጅቱ ገለጻ ከሆነ በትግራይ፤ በአፋር እና በአማራ ክልሎች 7 ሚሊዮን ዜጎች የረሀብ አደጋ እንዳያጋጥማቸው የአስቸኳይ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ 13 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች የአስቸኳይ ምግብ ድጋፍን እንደሚፈልጉ ድርጅቱ ደብሊው ኤፍ ፒ ከሶስት ሳምንታት በፊት ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።
የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት 426 ሚሊየን ዶላር እንደሚያስፈልገው የገለጸው ድርጅቱ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግለትም ጠይቋል፡፡