የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ጥቃቱ “በተደረገው ጥናትና ባገኘነው ጥብቅ መረጃ” መሰረት በታጠቀ ኃይል ላይ ያነጣጠረ ነበር ብሏል
በትግራይ ባለፈው ሰኔ 15፣2013ዓ.ም በተፈጸመ የአየር ጥቃት ንጹሃን ሰዎች ኢላማ ሆነዋል የሚል ሪፖርቶች በተለያዩ ተቋማቶች ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እና አሜሪካ በአየር ጥቃቱ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውንና ጥቃቱንም እንደሚያወግዙ ገልጸዋል፡፡
ነገርግን የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጦ፤በጥቃቱ ንጹሃን አለመጎዳታቸውን አስታውቋል፡፡
የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ቶጎጋ በተባለ የትግራይ መንደር ተፈጽሞ ለበርካታ ንጹሃን ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን የአየር ጥቃት በጽኑ እንደሚያወግዙ አስታውቀዋል፡፡ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን የተመኙት ዋና ጸኃፊው በጉዳዩ ገለልተኛና ፈጣን ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዋና ጸኃፊው ሁሉም አካላት በአለም አቀፍ ሰብአዊ መብትና የሰብአዊ መብት ስር ያላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡና ንጹሃንን እንዲጠብቁ አስገንዝበዋል፡፡ አንቶኒ ጉተሬዝ ውያው እንዲቆምና ግጭት በሰላም በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአሜሪካ መንግስት አዲስ አበባ በሚገኘው ኢምባሲው በኩል ባወጣው መግለጫ በትግራይ የገበያ ስፍራ በደረሰ የአየር ድብደባ በርካታ ንጹሃን መሞታቸውንና መቁሰላቸውን የሚያሳይ ሪፖርት እንደደረሰውና በጽኑ እንደሚያሳስበው ገልጿል፡፡
መግለጫው “ይህን ተቀባይነት የሌለው ነገር በጽኑ እናውዛለን” ብሏል፡፡ መግለጫው የህክምና ባለሙያዎች የድብደባውን ተጎጅዎች ለመርዳት በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የጽጥታ ሃይሎች ክልከላ ማድረጋቸውን ታዓማኒ ሪፖርት እንደደረሰው ጠቅሷል፡፡
በጉዳዩ ላይ “አስቸኳይና ገለልተኛ” ምርመራ እንዲደረግ የጠየቀው መግጫው መንግስት ተጎጅዎች ህክምና እንዲያገኙ እንዲፈቅድ ጥሪ አቅርቧል፡፡ አሜሪካ አሁንም በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግና የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስና ለንጹሃን ከለላ እንዲደረግ እንደምትፈልግ መግለጫው አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቃል አቀባይ ኮ/ል ጌትነት አዳነ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የአየር ጥቃቱ መፈጸሙን ያረጋገጡ ሲሆን በጥቃቱ ንጹሃን ሰዎች ጉዳት አልደረሰባቸውም ብለዋል፡፡
የአየር ጥቃቱ የተካሄደው “በተደረገው ጥናትና ባገኘነው ጥብቅ መረጃ” መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ ጥቃቱ ያነጣጠረው የታጠቀ ሓይል ላይ ነው፤ውጤታማም ነበር ብለዋል፡፡ ጥቃቱ የገበያ ቦታ ላይ ያለጣጠረ ነው የሚለውን ሪፖርት ሀሰት መሆኑና ጥቃቱ የተፈጸመው ገበያ ከተበተ ከ9ሰአት በኋላ ነው ብለዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ኮ/ሌ ጌትነት ጥቃቱ ያነጣጠረው” የሰማእታት ቀን እናከብራለን ሲል በነበረ ኃይል ላይ ነው” ፤የህወሓት ኃይሎች “ሲንቀሳቀሱ የትግራይ ሰራዊት ሲጠቁ የትግራይ ሲቪሊያን[ ንጹሃን] የሚሆኑበት እድል የለም” ብለዋል፡፡
ትግራይ ክልል ውስጥ ግጭት የተቀሰቀሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ክልሉን ሲመራ የነበረው ህወሓት በሰሜን እዝ ጥቃት ማድረሱን አሳውቀው፣ በህወሓት ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ ነበር።
ግጭቱን ተከትሎ ግድያን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በግጭቱ ተሳታፊዎች መፈጸሙን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና አለምአቀፍ የመብት ድርጅቶች ድምጽ ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡
የፌደራል መንግስት እርምጃውን የ“ህግ ማስከበር ዘመቻ” ያለው ሲሆን ህዳር 19 የትግራይን ዋና ከተማ መቀሌን መቆጣጠሩንና ዘመቻው ማብቃቱን አስታውቆ ነበር፡፡ ነገርግን በክልሉ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አልተረጋጋም፤ውጊያውም እስካሁን ሊቀጥል ችሏል፡፡
ህወሓት ባለፈው ግንቦት ወር መጀመሪያ “ሀገረመንግስቱን አደጋ” ላይ የሚጥል ተግባር ፈጽሟል በሚል ምክንያት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በአሸባሪነት ተፈርጇል፡፡
ተመድና አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ተቋምት ተኩስ ቆሞ ድርድር እንዲካሄድ ቢጠይቁም፣የኢትዮጵያ መንግስት በተወካዮች ም/ቤት በአሸባሪነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር በፍጹም እንደማይደራደርና ከ”አሸባሪው” ህወሓት ጋር “በእኩል ደረጃ መታየቱ እንደሚያበሳጨው” ማስታወቁ ይታወሳል፡፡