“ኢትዮጵያ ፓይለቶችን በማሰልጠን ትልቅ ድጋፍ ያደረገችልን ታሪካዊ ወዳጃችን ናት”- በኢትዮጵያ የአንጎላ አምባሳደር
አንጎላ ከፖርቹጋል የቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነጻ የወጣችው የዛሬ 46 ዓመት፤ በፈረንጆቹ 1975 እንደነበር ይታወሳል
የኢትዮጵያን ሁኔታ በተመለከተ “የየትኛውም ሀገር ማንኛውም ችግር የሚፈታው በሀገሪቱ ዜጎች ነው” ብሏል አምባሳደሩ
ኢትዮጵያ እና አንጎላ የቆየና ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው፡፡ አንጎላ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ከከፈተችበት ከፈረንጆቹ 1979 አንስቶ ሁለቱም ሀገራት በተለያዩ መስኮች በትብብር ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
ይህን በመሰለው የሃገራቱ ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ከአል-ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የአንጎላ አምባሳደር ፍራንሲስኮ ጆሴ ዳ ክሩዝ “ኢትዮጵያ የአንጎላ ፓይለቶችን በማሰልጠን ትልቅ ድጋፍ ያደረገችልን ታሪካዊ ወዳጃችን ናት” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የራሷ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ለማልማት የያዘቸው አቋም በቴክኖሎጂው ዘርፍም ነፃ ሀገር መሆኗን ለማሳየት ነው- ዶ/ር ሹመቴ ግዛው
ሀገራቱ በአቪዬሽን የጀመሩት የትብብር ማእቀፍ እንደፈረንጆቹ ከ2019 ወዲህ ወደ ቴክኒካል ደረጃ አድጎ በተለያዩ መስኮች በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙም አምባሳደሩ አንስተዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ደረጃ የፖለቲካ ምክክር እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡
ግብርና፣ ማዕድን እና ቱሪዝም ሀገራቱ በጋራ ሊሰሩ የሚችሉባቸው የትብብር ማእቀፎች እንደሆኑም ጠቁመዋል አምባሳደሩ፡፡
አምባሳደር ፍራንሲስኮ ጆሴ ዳ ክሩዝ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታን በተመከተ ከአንጎላ ያለፈ ታሪክ ጋር በማስተሰሰር አስታየየታቸውን ሰንዝሯል፡፡
ሱዳን፤ አስገዳጅ ሁኔታ እስካልገጠማቸው ድረስ ዜጎቿ ኢትዮጵያን ለቆ ለመውጣት እንዲዘጋጁ አሳሰበች
አንጎላ በፈረንጆቹ ህዳር 11/1975 ነጻነቷን ብትቀዳጅም እርስ በራሳቸው የሚፋለሙ የተለያዩ ታጣቂ ኃይሎች የነበሩባት፣ የተከፋፈለች እንዲሁም ከ1975 እስከ 2002 ከባድ ግጭት ያስተናገደች ሀገር እንደነበረች ያስታወሱት አምባሳደሩ፤ “በ2002 በሀገሪቱ በተከፈተው አዲስ ምዕራፍ እና አመራሩ በወሰደው ቁርጠኛ እርምጃ ሁሉም የአንጎላ ኃይሎች ባሳተፈ መልኩ በሀገሪቱ ተጋርጦ የነበረውን አደጋ ሊቋጭ ችሏል” ብለዋል፡፡
አሁን በአንጎላ የሚታየው ሰላም እና መረጋጋት እንዲመጣ ሁሉም አንጎላውያን የሀገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም፣ ሉዓላዊነት እና አንድነት ባስጠበቀ መልኩ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውንም ነው ዳ ክሩዝ ያነሱት፡፡
የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ በሰጡት አስተያየትም “የየትኛውም ሀገር ማንኛውም ችግር የሚፈታው በሀገሪቱ ዜጎች ነው” ብለዋል፡፡
ማንኛውም ግጭት ሁሉንም ኃይሎች ባሳተፈ እና የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚቻልም ነው አምባሳደሩ የተናገሩት፡፡
“ማንም ሰው የሌላውን ሀገር ችግር ሊፈታ አይችልም፤ ችግሩን መፍታት የሚችሉት የዛች ሀገር ዜጎች ብቻ ናቸው፡፡ እኛ ከነጻነት በኋላ የተረከብናት የተከፋፈለች አንጎላን አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ ለማድረስ የሄድንበት መንገድ ይህ ነው” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
አንጎላ ቀጣናዊም ሆነ አህጉራዊ ኃላፊነቶችን ለመወጣት የበኩሏን ድርሻ እየተጫወተች እንደሆነም ነው አምባሳደሩ ያነሱት፡፡
“የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ተጠፍጥፎ የሚቀመጥለትን አሻንጉሊት መንግስት አይቀበልም”- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት
ካሳለፈችው ፈተና እና ካላት ልምድ አንጻር በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ፈተና በገጠማቸው ጊዜ ከጎናቸው ስትቆም መቆየቷን በማከልም፤ አሁንም ቢሆን ያላትን ስኬታማ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መነሻ በማድረግ የቀጣናውም ሆነ የአህጉሪቱ ሰላም እንዲረጋገጥ ኃላፊነቷን እየተወጣች እንደምትገኝ ጠቁመዋል፡፡
“በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ፤ አንጎላ የበኩሏን ሚና እየተጫወተች ትገኛለች” ሲሉም በማሳያነት አንስተዋል አምባሳደሩ፡፡
ዳ ክሩዝ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት በአህጉሪቱ የሚታዩ ግጭቶች እንዲያበቁ የበኩላቸው ድርሻ እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
አንጎላ ከፖርቹጋል የቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነጻ የወጣችው የዛሬ 46 ዓመት፤ በፈረንጆቹ 1975 እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ኃብት እንዳላት የሚነገርላት አንጎላ እንደፈረንጆቹ ከ1975 እስከ 2002 ተከስቶ በነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት ኢኮኖሚዋን ክፉኛ ቢዳከምም፤ አሁን በከፍተኛ ሁኔታ እያንሰራሩ ካሉ ሀገራት መካከል ትጠቀሳለች፡፡