ከሕገወጥ የወርቅ ምርትና ግብይት ጋር በተያያዘ 32 አመራሮች ተያዙ
ኢትዮጵያ ከቀናት በፊት 29 የውጭ ሀገራት ዜጎችን በህገወጥ የወርቅ ግብይት ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል ማሰሯ ይታወሳል
የሶስት ክልል አመራሮች በህገወጥ የወርቅ ግብይት ወንጀል ተጠርጥረው ታስረዋል ተብሏል
ከሕገወጥ የወርቅ ምርትና ግብይት ጋር በተያያዘ 32 አመራሮች ተያዙ።
በሕገወጥ የወርቅ ምርት፣ ግብይትና ዝውውር ተሳትፎ ነበራቸው የተባሉ 32 የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የጸጥታ መዋቅር አመራሮችና አምራቾች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ ወርቅ ሲያመርቱ፤ ሲያዘዋውሩ፣ በጥቁር ገበያ ሲሸጡ እንዲሁም ከውጭ ሀገራት ዜጎች ጋር የጥቅም ትስስር ፈጥረው የሀገርን ጥቅም ሲጎዱ ነበር ተብሏል።
- የኢትዮጵያ ፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በሙስና ተጠርጥረው ተያዙ
- በወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩ ሰዎች ለዋስትናና ለምርመራ የተያዙ ገንዘቦችና ንብረቶች ለምን በጊዜው አይመለሱም?
በቁጥጥር ስር ከዋሉት 32 ግለሰቦች መካከልም ስምንቱ የመንግሥትና የጸጥታ መዋቅር አመራሮች ሲሆኑ፤ ሰባቱ ደግሞ ሕጋዊ ፈቃድን ሽፋን አድርገው በሕገወጥ መንገድ ሲሠሩ የነበሩ አምራቾች እንዲሁም 17 አዘዋዋሪዎችና በሕገወጥ ድርጊቱ የተለያየ ተሳትፎ ያላቸው መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በዚህም ከ15 ቀን በፊት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በሕገወጥ የወርቅ ምርትና ግብይት ተግባር ተሰማርተው የተገኙ 29 የውጭ ሀገራት ዜጎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል፡፡
በጋምቤላና በደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልልም በተመሳሳይ ሕገወጥ ድርጊት የተሰማሩ ግለሰቦች መያዛቸው ተገልጿል።
በሕገወጥ የወርቅ ምርት ግብይትና ዝውውር ተሳትፎ የነበራቸው የመንግሥት ኃላፊዎችና የጸጥታ መዋቅር አመራሮች የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ ወደ ጎን በመተው በወርቅ ማምረትና ዝውውር ውስጥ በቀጥታ ተሳትፎ ነበራቸው ተብላል።
አንዳንዶቹ የመንግሥት ሥልጣንና ኃላፊነትን እንደ ከለላ በመጠቀም የወርቅ ማምረትንም ሆነ ዝውውሩን አጣምረው በማካሄድ የሀገር ሀብት ሲዘርፉ መቆየታቸው እንደተደረሰበት በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡
በዚህ ወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩት መካከልም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኩምሩክ ወረዳ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ፅ/ቤት ኃላፊ ከማል መሀመድ፣ የግብርና ፅ/ቤት ኃላፊ አብዱልከሪም ዬሚዳ፣ የወረዳው ፖሊስ አመራር ም/ኮ አብዱልሙንየም ሱሌማን እንዲሁም ምክትል አስተዳዳሪ የነበረው አሳይድ አልዕግብ በቁጥጥር መዋላቸው ተገልጿል፡፡
በጋምቤላ ክልል ደግሞ የዲማ ወረዳ ማዕድን ፅህፈት ቤት ኃላፊ የሆነው ኡቦንግ ኡቶው ኡጉድ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የምዕራብ ኦሞ ዞን የቤሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ከበደ ቡርጂ እና ሌሎችም ከሕገወጥ ድርጊቱ ጋር ትስስር የነበራቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብላል ሲል ፋና ብሮድካስቲንግ ዘግቧል።
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ 21 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከ420 መሰል ጥይቶች፣ 14 ሽጉጦች ከ62 መሰል ጥይቶች፣ 2 ኤፍ1 ቦምቦች፣ 250 የብሬን ጥይቶች፣ ወርቅ፣ 8 የወርቅ ሚዛን፣ 5 የወርቅ መፈተሻ ማሽን፣ 2 የወርቅ ማቅለጫ እንዲሁም የተለያዩ የወርቅ ናሙናዎች፣ ኬሚካሎች እንዲሁም በርካታ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችና የባንክ ደብተሮች በኤግዚብትነት መያዛቸው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።