ከሰሞኑ በሸዋሮቢትና በአካባቢው በተቀሰቀሰው ግጭት ምን ያህል ጉዳት ደረሰ?
ግጭቱን ተከትሎ ወደ ደሴ የሚያልፈው ዋናው የሰሜን ኢትዮጵያው መንገድ ተዘግቶ እንደነበር ይታወሳል
ዳግም አገርሽቶ ጥቂት የማይባሉ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ግጭት መርገቡን ተከትሎ ተሽከርካሪዎች እያለፉ ነው
ከትናንት በስቲያ እሁድ ከሰዓት መልስ ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አጎራባች አካባቢዎች የተሰቀሰው ግጭት ቆሟል፡፡
በጦር መሳሪያ የታጀበው ግጭት ሚያዚያ 9 ቀን 2014 ዓ/ም ነበር ከቀኑ 09፡00 አካባቢ በዞኖቹ አጎራባች አካባቢዎች የጀመረው፡፡ የኤፍራታና ግድም፣ የቀወት እና የጅሌ ጥሙጋ ወረዳዎች አካል የሆኑ አካባቢዎችንም አዳርሷል፡፡ ከአጣዬ በቅርብ ርቀት የሚገኙ ሞላሌ፣ ጀጋኖ፣ ባልጪ እና ጀጀባ የሚባሉ አካባቢዎችን ጨምሮ ሸዋሮቢት ከተማ የግጭቱ ማዕከላት ነበሩ፡፡
በተለይም ዙጢ ተብሎ በሚጠራው የሸዋሮቢት ከተማ አካባቢ ሲካሄድ የነበረው ውጊያ የከተማውን ህዝብ ለሽብር እና መኖሪያውን ለቆ እንዲወጣ ጭምር ያስገደደ ነበረ እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ፡፡
በሰሜን ሸዋ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን በሲቪል ሰዎች ላይ ባነጣጠሩ ጥቃቶች የብዙ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ኢሰመኮ ገለፀ
በግጭቱ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ አል ዐይን የጠየቃቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በሁለቱም ወገን ከ30 የበለጡ ሰዎች ህይወት ማለፉንና በርካቶች መቁሰላቸውን ተናግረዋል፡፡ ልዩ ኃይል እና ፋኖን ጨምሮ 9 ሰዎች ገደማ መሞታቸውን ያረጋገጡልን ነዋሪዎችም አሉ፡፡
አል ዐይን አማርኛ ወደ ሸዋሮቢት ጤና ጣቢያ ከገቡ ተጎጂዎች የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉንና አምስት ሰዎች መጎዳታቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ አግኝቷል፡፡ ወደ ጤና ጣቢያው ያልመጡ ተጎጂዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የገለጹልን የጤና ጣቢያው ምንጮች ሌሎች ሶስት ሰዎች መሞታቸውንም ነው የገለጹልን፡፡
ሆኖም አል ዐይን የሟቾቹን ቁጥር በተመለከተ ትክክለኛውን ቁጥር ለማግኘትም ሆነ ለማረጋገጥ አልቻለም፡፡
ስለ ጉዳቱ የጠየቅናቸው የአካባቢው ባለስልጣናትም ገና በመጣራት ላይ ነው በሚል ቁጥሩን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በኩል 10 ሰዎች መሞታቸውንና 42 ገደማ ሰዎች መቁሰላቸውን የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ መሐመድ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
በግጭቱ በተለይ ወሰን ቁርቁር ተብሎ ከሚጠራው የወረዳው ቀበሌ በርካቶች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውንም ነው ዋና አስተዳዳሪው የተናገሩት፡፡
አቶ አህመድ ግጭቱ ህዝብን እንደማይወክል የተናገሩም ሲሆን በሁለቱም ወገን ያሉና የተለየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው አካላት አካባቢውን ለተደጋጋሚ ግጭት እንደዳረጉት ገልጸዋል፡፡
አሁን ያለፉትን ሁለት ቀናት የነበረው ግን ግጭቱ ቆሟል፡፡ ሰላማዊ ቀን ማለፉንም ነው ነዋሪዎች የገለጹልን፡፡ በዚህም ለጊዜው ከሸዋሮቢት ወጥተው የነበሩ ነዋሪዎች እየተመለሱም ይገኛሉ፡፡
ግጭቱ የክልሉ ልዩ ኃይል በመሃል ገብቶ መስፈሩን ተከትሎ መቆሙን የገለጹልን የቀወት ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ አሳሳኸኝ በአመራሮች ደረጃ ምክክር እየተደረገ መሆኑን ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
በዞንና በወረዳ ደረጃ ባሉ አመራሮች ደረጃ ምክክር ተደርጎ ግጭቱን በማስቆም መነሻው ላይ ለመወያየት የአካባቢውን ህዝብ ለማወያየት ስምምነት ላይ መደረሱንም ነው የገለጹት፡፡
ምክትል አስተዳዳሪው ወደ ስራ ለመግባት የሚያስችለንን ስራ ተከፋፍለን ተለያይተናነልም ነው ያሉት፡፡
የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ አካላት ገብተው ግጭቱ መርገቡን የነገሩን የጅሌ ጥሙጋ ዋና አስተዳዳሪው አቶ አህመድም አርሷደራችንን አወያይተን ወደ ቤቱ እንዲመለስና ሰላም እንዲሰፍን አድርገናል ብለዋል፡፡
በቀጣይ የሃገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት አባቶችን እንዲሁም ወጣቶችን ጭምር በማሳተፍ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት በዞንና በወረዳ ደረጃ ስምምነት ላይ መደረሱንም ነው የገለጹልን፡፡
አጣዬ ከተማ በታጣቂዎች ጥቃት “ሙሉ በሙሉ መውደሟ” ተገለፀ
የሰሜን ሸዋ ዞን የጸጥታና አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ብርሃኑም ግጭቱ ቆሞ ሰላም መስፈኑን በመግለጽ የደረሰው ሰብዓዊና የንብረት ጉዳት በመጣራት ላይ መሆኑን ነግረውናል፡፡
ጉዳቱን ከማጣራቱ ጎን ለጎን አጥፊዎችን በመለየት በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም ነው አቶ ዋሲሁን የነገሩን፡፡
የግጭቱን መቆም ተከትሎም ወደ ደሴ እና ወደ ሌሎች የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚያመራው ዋና መንገድ ተከፍቷል፡፡ ተሽከርካሪዎች ማለፍ መጀመራቸውንም ነው አቶ ዋሲሁን ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩት፡፡
ሆኖም የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም ስጋት አላቸው፡፡ በድጋሚ ልንጠቃ እንችላለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡
አካባቢው ለመሰል ጥቃቶች ተደጋግሞ መጋለጡን ተከትሎ ግጭቱ ዳግም ላለማገርሸቱ ምን ዋስትና እንዳለ እና ዘላቂ መፍትሔው ምን እንደሆነ አል ዐይን የጠየቃቸው አቶ ዋሲሁን የግጭቱ መቆም ከተረጋገጠ በኋላ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የማጠናከርና ዘላቂ ሰላምን የማስፈን ስራዎች እንደሚሰሩ መልሰዋል፡፡
ሆኖም ከበላይ ያሉ የአመራር አካላት ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነና እንደሚጠበቅም ጭምር አቶ ዋሲሁን አልሸሸጉም፡፡
አል ዐይን ግጭቱን በማስመልከት የአማራ ክልል ባለስልጣናትን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡