ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም ምስክርነታቸው ቀርቶ ፍርድ ቤት ቀረቡ
በዚህም ከእስር እንዲለቀቁና አስፈላጊው የምስክርነት ጥበቃ እንዲደረግላቸው አዝዞ ነበረው አቃቤ ህግ ትዕዛዙን ማንሳቱን አስታውቋል
በእነ አቶ ስብሐት ነጋ ላይ ለመመስከር ተስማምተው ነበር የተባለላቸው ወ/ሮ ኬሪያ ምስክርነታቸው ቀርቷል ተብሏል
የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም የምስክርነት ጥበቃቸው ተነስቶ ዳግም ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ገለጸ።
ወይዘሮ ኬሪያ ዛሬ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የፕሬስ ሴክሬቴሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን ለኢዜአ እንደገለጹት ወይዘሮ ኬሪያ ከተከሳሽነት ወደ ምስክርነት ተቀይረው ነበር።
ተጠርጣሪዋ በጠቋሚዎችና ምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 በገቡት ሥምምነት መሠረት ዝርዝር የምስክርነት ቃላቸውን በፈቃዳቸው መስጠታቸውን አስታውሰዋል።
በገዛ ፈቃዳቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተው እንደነበር ያስታወሱት አቶ አወል በፍርድ ቤት ውሳኔ ከእስር እንደተለቀቁና ጎን ለጎንም ለግለሰቧ አስፈላጊውን የምስክርነት ጥበቃ ሲደረግላቸው መቆየቱን ተናግረዋል።
ይሁንና ወይዘሮ ኬሪያ ቆይተው ምስክር መሆን ፍላጎት እንደሌላቸው እንዲሁም ምስክርነት ሲሰጡ የቆዩት ተገደው እንደነበር በመግለጻቸው ምስክርነታቸው ማቋረጡን ገልጸዋል።
በምስክሮችና ጠቋሚዎች አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 11 መሰረት የጥበቃ ተጠቃሚው ሥምምነቱንና ግዴታውን የማያከብር ከሆነ የጥበቃ ስምምነት ውሉ ይቋረጣል።
ይህንንም ተከትሎ አቃቤ ሕግ ለወይዘሮ ኬሪያ ምስክር በመሆናቸው ይሰጣቸው የነበረውን ጥበቃ ለማንሳት መገደዱን ነው አቶ አወል የተናገሩት።
ከዚህም በኋላ ወይዘሮ ኬሪያ ከዚህ ቀደም በተጠረጠሩበት ወንጀል የቅድመ ምርመራ ስራ እንዲጀመር አቃቤ ሕግ ዛሬ ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቧል ብለዋል።
የተጠርጣሪዋ ጠበቆች በጉዳዩ ላይ ለመከራከር አልተዘጋጀንም በማለታቸው ፍርድ ቤቱ ወ/ሮ ኬሪያ በመጪው ሰኞ ዳግም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡና እስከዚያው በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲቆዩ አዟል።
ወ/ሮ ኬሪያ አቶ ስብአት ነጋን ጨምሮ በ42 ተጠርጣሪዎች ላይ ምስክርነት ለመስጠት በራሳቸው ፍቃድ ተስማምተዋል ሲባል እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
የቀድሞዋ አፈ ጉባዔ ህዳር 22 ቀን 2013 ዓ/ም እጃቸውን ለመንግስት መስጠታቸውም አይዘነጋም።