ህወሓት ተደራዳሪ ለመላክ መወሰኑን ገልጿል
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር የተፈረጀውና ትግራይን እያስተዳደረ ካለው ህወሃት ጋር ንግግር ሊያደርግ መሆኑን መንግስት ገልጿል።
ትናንትና ለምክር ቤተር አባላት ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማምጣት ያለመ ኮሚቴ በም/ጠ/ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ እየተመራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ወሃትም በአንጻሩ በኬንያ ድርድር ለማድረግ መስማማቱንና ተደራዳሪ ወደ ስፍራው እንደሚልክ ሊቀመንበሩ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል አስታውቀዋል።
ከሰሞኑ በታንዛኒያ፣ በኬንያ፣ እንዲሁም በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች መንግስትና ህወሃት ሊደራደሩ እንደሆነ ቢነገርም መንግስት ግን ይህንን ወደፊት ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።
ሁለቱ ወገኖች በድርድሩ ቢስማሙም የድርድሩ ተሳታፊዎች እነማን መሆን አለባቸው በሚለው ላይ የተለያዩ ሃሳቦች እየተነሱ ነው።
ትናንት የምክር ቤት አባሉ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በድርድሩ የአማራ ክልል እና የኤርትራ መንግስት መሳተፍ እንዳለባቸው ቢጠይቁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግን ህወሃት የአማራ ጠላት ብቻ አይደለም፤ አማራ ብቻ ይደራደር ከተባለ አማራ ብቻ ይዋጋ የሚል ሃሳብ ሰጥተዋል።
የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ሙሳ አደም ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራው ቆይታ ጦርነቱ ሁሉንም አካል የሚመለከት በመሆኑ አካታች ድርድር መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያው ዘላለም ሞገስ (ዶ/ር) ማንኛውም የሰላም ድርድር ውጤታማና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያመጣ አካታች መሆን እንዳለበት ገልጸው ለዚህም የአማራና የአፋር ክልሎች የድርድሩ አካል መሆን እንዳለባቸው አንስተዋል።
አሁን ላይ ግን ሁለቱ ክልሎች እየተሳተፉ እንደሆነ የሚያመለከት ነገር አለመኖሩን ያነሱት አስተያየት ሰጭው፤ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ ተወካይ በመጀመሪያዎቹ የሹመት ወራት ሁለቱንም ክልሎች ማነጋገራቸው በማስታወስ፤ አሁን ግን በዋናነት ከፍተኛ ተወካዩ የፌዴራል መንግስቱና ህውሃት ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጋቸውን አንስተዋል።
የአማራና አፋር ክልሎች በፌዴራሉ መንግስት ይወከላሉ ከሚል እሳቤ በመነጨ ክልሎቹ በድርድሩ እንዳይሳተፉ ማድረግ ትክክል አለመሆኑን የሕግ ምሁሩ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ የተካረረ የፓለቲካ ምህዳር፤ ሴራና ግመታ እውነት ተደርገው እየታዩ በመሆኑ ሁለቱን ክልሎች በሚገባው ልክ የማያሳትፍ ድርድር ካለ የሌላ ጦርነት መሰረት የማስቀመጥ አጋጣሚው ሰፊ እንደሆነም ነው ዶ/ር ዘላለም የተናሩት።
የአፋር እና አማራ ክልሎች መንግስታት በድርድሩ የማይሳተፉ ከሆነ የቅቡልነት ችግር ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉም ነው ያነሱት፡።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት ረዳት ፕ/ር ተሰማ በላይ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በድርድር ለመፍታት በአፍሪካ ህብረት በኩል በሚደረገው ጥረት ማን ይሳተፍ የሚለው ጥያቄ ራሱ የድርድሩ አካል ተደርጎ መታየት እንዳለበት ተናግረዋል።
ይጀመራል የተባለው ድርድር ከፖለቲካ መድረክ ወጥቶ በጦርነት አውድማ ለመፍታት እየተሞከረ የነበረን ቀውስ ወደ ፖለቲካና ዲፕሎማሲ ማዕቀፍ ለመመለስ የሚደረግ በመሆኑ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ህገ መንግስትም ሆነ ሌሎች ህጎች መሰረት የሚደረግ እንዳልሆነም የሕግ መምህሩ ይናገራሉ።
ህወሃት በሽብርተኝነት ተፈርጆ፣ አመራሮቹም የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ቢሆንም፤ ጦርነቱ እየተባባሰ ስለሄደና ችግሩን ፌደራል መንግስት መጀመሪያ በያዘው ህግ የማስከበር ማዕቀፍ መፍታት ስላልተቻለ የድርድር አማራጭ መሞከሩ አስፈላጊ እንደሆነም ረዳት ፕ/ር ተሰማ በላይ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል።
ከጦርነት ለመውጣት በሚደረግ ድርድር ጉዳዩ የሚመለከታቸው በሙሉ መካተት ለድርድር ሂደቱ መሳካትና ለውጤቱም ተቀባይነት ሰፊ ሚና የሚጫወት እንደሆነም ገልጸዋል። በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሂደት ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች በቀጥታ እንደተጎዱ የታወቀ ስለሆነ በድርድሩ መሳተፍ እንዳለባቸው ነው ምሁሩ የተናገሩት፡፡
አማራ እና አፋር ክልሎች በኢትዮጵያ በኩል ስለሚወከሉ የግድ በክልል ደረጃ መወከል አለባቸው?
ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያው ዘላለም ሞገስ (ዶ/ር) አማራ እና አፋር ክልሎች በድርድሩ ካልተሳተፉ መንግስትን አጣብቂኝ ውስጥ ሊያስገባው እንደሚችል ገልጸዋል።
ሁለቱም የክልል መንግስታት በድርድሩ የሚሳተፍ ወኪል ሊኖራቸው እንደሚገባ ያነሱት የህግ ምሁሩ ጦርነቱ የተደረገው በፌዴራልና በትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን በትግራይና አፋር እንዲሁም በትግራይና አማራ ጭምር በመሆኑ መሳተፍ አለባቸው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ የሰላም ኮሚቴ መኖሩን የገለጹ ቢሆንም እርሳቸው የፌዴራል መንግስት ባለስልጣን እንጅ የክልል ባለስልጣን ባለመሆናቸው ክልሉ ሌላ ተወካይ ያስፈልገዋል ብለዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን ከአማራ ክልል ናቸውና ክልሉን ወክለው ይደራደሩ ከተባለ የመከላከያ ሚኒስተሩ ዶ/ር አብርሃም በላይም ትግራይን ወክሎ ሊሳተፍ ይችላል እንደማለት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከአፋርና አማራ የተቀዋሚ ፓርቲ አባላትና ምሁራን ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ ቢሳተፉ መልካም እንደሆነም ነው ዶ/ር ዘላለም ያነሱት። ከትግራይ ጋር የሚኖረው ድርድር የሚነካቸው አጀንዳዎች ሌላውንም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመለከት የመሆን አጋጣሚው ሰፊ መሆኑንም ነው ያነሱት።
አሁን ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው ድርድር በጥቂት ሰዎች ተጀምሮ በጊዜ ሂደት ሌሎችን እያሳተፈ እንዲሄድ ማድረግ እንደሚገባምና ይህንን ማድረጉም ለሰላም ሂደቱ ቅቡልነት ወሳኝ ነገር ነው ተብሏል።
ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው ድርድር ዙሪያ የአማራ ክልልም ይሁን የአፋር ክልል እስካሁን የሰጡት አስተያየት የለም።