ህወሓት በረራዎችን አግዶ እርዳታዎችን አስተጓጉሏል መባሉን አስተባበለ
መንግስት ዛሬ በሰጠው መግለጫ ህወሃትን እርዳታዎችን እያስተጓጎለ ነው ሲል ከሶ ነበር
ድርጁቱ የመቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ በነዳጅ እጥረት ምክንያት ስራ አቁሟል ሲል መግለጫ አውጥቷል
ህወሓት የመቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ በነዳጅ እጥረት ምክንያት አገልግሎት ማቆሙን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መንግስት ህወሓት የእርዳታ አውሮፕላኖች እንዳያርፉ አድርጓል ሲል እርዳታዎችን እያስተጓጎለ ነው በሚል ከሶ ነበር።
ሆኖም የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ክሱን አስተባብለው በይፋዊ የትዊተር የማህበረሰብ ገጻቸው ምላሽ ሰጥተዋል።
ህወሓት የውጭ ጉዳዮችን የማስተባብርበት ነው የሚለው ተቋምም ክሱን የተመለከተ መግለጫ አውጥቶ አስተባብሏል።
በማስተባበያው አቶ ጌታቸው ረዳም ሆኑ መግለጫው የመቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ በነዳጅ እጥረት ምክንያት አገልግሎት እንዳቆመ አስታውቀዋል።
በመቀሌ ያለው እውነታ እንደተባለው አይደለም ሲሉ ክሱን ያስተባበሉት የቡድኑ ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ አውሮፕላን ማረፊያው በጊዜያዊነት መዘጋቱን ገልጸው የዚህ ምክንያቱም የነዳጅ እጥረት ነው ብለዋል።
የመቀሌ አውሮፕላን ማረፊያን በመጠቀም ዕርዳታ ለማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከረድኤት ድርጅቶች ጋር እየተጋገሩ እንደሆነም ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት።
አቶ ጌታቸው አውሮፕላን ማረፊያው በቅርቡ ወደ አገልግሎት ይመለሳል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
"መንግስት፤ ህወሓት ዕርዳታ እንዳይገባ እንዳደረገ በማስመሰል በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በሌሎችም ቦታዎች የተደረጉ ግድያዎችን አጀንዳ ለማስቀየር እየሞከረ ነው" ሲሉም ነው ቃል አቀባዩ መልሰው የከሰሱት።
መንግስት "እያደረገው ያለው አጀንዳን የማስቀየር ድርጊት አሳዛኝ" እንደሆነም ገልጸዋል።
መንግስት ዛሬ ጠዋት በሰጠው መግለጫ ህወሓት አውሮፕላን አያርፍም በማለት ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን እያስተጓጎለ ነው ሲል መክሰሱ ይታወሳል።
ህወሓት የነዳጅ እጥረት አጋጥሟል ማለቱን "ውሸት" ሲል ያጣጣለው መንግስት ተዋጊዎቹን ለማንቀሳቀስ በማሰብ የፈጠረው ወሬ እንደሆነ ማስታወቁም አይዘነጋም።
የተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ሲል ህወሓትን መፈረጁም የሚታወስ ነው።