ተወካዩ ከህወሓት በተጨማሪም ከም/ጠ/ሚ/ር ና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ጋር ተገናኝተዋል
የአውሮፓ ህብረት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና ከህወሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ጋር ተገናኙ፡፡
ኮሚሽነር ዣኔዝ ሌናርቺች በአዲስ አበባ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር፤ በመቀሌ ደግሞ መንግስት በሕግ ከሚፈልጋቸው የህወሃት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡
የሕወሓት ሊቀመንበር ከአውሮፓ የቀውስ ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔዝ ሌናርሲች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት ሌላው ሕግ የሚፈልጋቸው የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ናቸው፡፡
ኮሚሽነር ጄኔዝ ሌናርሲች ቀደም ብለው በመቀሌ ከተማ የሚገኘውን የአይደር ሆስፒታልን መጎብኘታቸውንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
ከኮሚሽነሩ ጋር ውይይት ያደረጉት ም/ ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ላላት አጋርነት ትልቅ ትኩረት እንደምትሰጥ መናገራቸውን መስሪያ ቤታቸው ገልጸዋል፡፡
አዲስ አበባ ከኮሚሽኑ እና ከአባል ሀገራቱ ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር እየሰራች መሆኑንም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስታወቀው፡፡
አቶ ደመቀ ፤ ለትግራይ ክልል የሚደርሰው ዕርዳታ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሳምንት 500 የጭነት መኪኖች እየሄዱ መሆኑን ገልጸው፤ አጋር አካላት የአማራ እና አፋር ክልሎችንም ጨምሮ ለተጎዱ ወገኖች የሚደረገውን ድጋፍ እንዲያፋጥኑ መጠየቃቸው ተገልጿል፡፡
ኮሚሽነር ዣኔዝ ሌናርቺች በበኩላቸው ነዳጅ፣ ጥሬ ገንዘብ እና ሌሎችም ድጋፎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲሄዱ ጥሪ ማቅረባቸው ተገልጿል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ህብረት መሪነት በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በኩል እየተደረጉ ያሉ የሰላም ጥረቶች ላይ ያለውን ሁኔታ ለኮሚሽነሩ አስረድተዋል ተብሏል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሰላም ውጥኖች ላይ ህወሓት ያሳየውን አሳማኝ ያልሆነ “መጠራጠር አቋም” ለኮሚሽነሩ ነግረዋል ተብሏል፡፡ ኮሚሽነሩም ለአፍሪካ ህብረት ለሰላም ሂደቱ ያለውን ድጋፍ ገልፀዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና ኮሚሽነሩ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሰብዓዊ ድጋፍ ስለሚሹ ከ24 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ጉዳይም ምክክር አድርገዋል ተብሏል።
የአውሮፓ ህብረት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ዣኔዝ ሌናርቺች በትግራይና በሶማሌ ክልል ጉብኝት ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡