ከፍተኛ የሕወሓት አመራሮቹ ዛሬ በተከዜ ወንዝ ዳርቻ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ መገደላቸው ተገልጿል
የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች በዛሬው እለት በጋራ ባደረጉት ጠንካራ ፍተሻ ቀደም ሲል ሠራዊቱን በማስመታት ኢትዮዽያን ለማተራመስ ሲንቀሳቀሱ፣ ሲያቅዱና ሲመሩ የነበሩ ቀንደኛ የሕወሓት አመራሮች በተከዜ ወንዝ ዳርቻ መደምሰሳቸውን ለኢዜአ ገልፀዋል። ከጥበቃ ኃይላቸው ጋር በነበረው የተኩስ ልውውጥ በውጊያ ላይ ከነጥበቃዎቻቸውና የጥበቃ ወታደራዊ አመራሮቻቸው ጋር ነው መገደላቸው የተገለጸው፡፡
ዛሬ በነበረው ውጊያ ከጥበቃዎቻቸው ጋር አብረው የተደመሰሱ የሕወሓ አመራሮች፡-
1. አቶ ስዩም መስፍን: የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩ እንዲሁም ውጊያውን የመሩና ሰራዊቱ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ ያዘዙ፣ በመጨረሻም በሰራዊቱ ላይ ውጊያ እንዲከፈት ትዕዛዝ የሰጡ፣
2. አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ፡ የሕወሓት ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር የነበሩ
3. አቶ አባይ ፀሃዬ፡ የሕወሓት ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር የነበሩ
4. ኮሎኔል ኪሮስ ሀጎስ፡ ከመከላከያ የከዳ - ከነጥበቃዎቻቸው ናቸው፡፡
አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ
በሌላ በኩል በቁጥጥር ስር የዋሉ ወታደራዊና የክልል አመራሮች፡-
1. ኮሎኔል ገብረመስቀል ገብረ ኪዳን፡ ከመከላከያ የከዳ፣
2. ኮሎኔል ፍስሃ ብርሃኔ፡ ከመከላከያ የከዳ፣
3. ኮሎኔል ዘረአብሩክ ታደሰ፡ ከመከላከያ የከዳ፣
4. ኮማንደር ገብረኪዳን አስገዶም የልዩ ሀይል ክፍለ ጦር አዛዥ የነበረ፣
5. አቶ መብራህቶም ክንዴ ሀይሉ፡ የክልሉ ውሃ ስራዎች ድርጅት ፋይናንስ ኃላፊ የነበረ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የመከላከያ ሰራዊት ኃይል ስምሪት መምሪያ ሀላፊ ብርጋደል ጀነራል ተስፋዬ አያሌው፣ ባስተላለፉት መልዕክት፣ አሁንም በየዋሻው የተደበቁ የሕወሓት ቡድን አባላት በሰላማዊ መንገድ እጅ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።