ሌሎች በቁጥጥር ስር የዋሉ የሕወሓት አመራሮችም አብረው አዲስ አበባ ገብተዋል
የቀድሞውን የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አባይ ወልዱና ከሕግ ማስከበር እርምጃው በፊት ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትን አብርሃም ተከስተን (ዶ/ር) ጨምሮ “ሀገር ለመበታተን ሲሰሩ ቁጥጥር ስር የዋሉ የህወሓት ጁንታ አመራሮች” ዛሬ ጥር 03 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ገብተዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ጥምር ሃይል በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ ሀገር ለመበታተን ሲሰሩ ነበሩ የተባሉ የሕወሓት ቡድን አባላትን ለሕግ የማቅረብ ተልዕኮ እንደቀጠለ መሆኑ ተገልጿል።
በትናንትናው ዕለትም የቀድሞውን የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አባይ ወልዱና የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶክተር አብርሃም ተከስተን ጨምሮ ዘጠኝ የሕወሓትአመራሮች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ዶ/ር አብርሃም ተከስተ
የሕወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑትን ስብሃት ነጋ (አቦይ ስብሃትን) ጨምሮ እስካሁን በርካታ የሕወሓት አመራሮች እና ከመከላከያ ሠራዊት ከድተዋል የተባሉ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በቁጥጥር ስር ሲውሉ እርምጃ ተወስዶባቸው ለሞት የተዳረጉትም በርካታ ናቸው፡፡