በትግራይ ክልል “ከታህሳስ መጨረሻ ጀምሮ በተፈጸመ የአየር ጥቃት 108 ሰዎች መገደላቸውን” ተመድ አስታወቀ
ህወሓት በንጹሃን ላይ የአየር ጥቃት አድርሷል ሲል መንግስት ይከሳል፤መንግስት ክሱን አይቀበለውም

ከሞቱት ሰዎች “59ኙ በመጠለያ ጣብያ የነበሩ ተፈናቃዮች የነበሩ መሆናቸው ጥቃቱ አስከፊ አድርጎታል” ተብሏል
በሰሜን ኢትዮጰያ ትግራይ ክልል በተፈጸመ የአየር ጥቃት፤ በዚህ ወር ብቻ 108 ሰዎች መሞታቸውን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መብቶች ቢሮ አስታወቀ፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ቢሮ ቃል አቀባይ ሊዝ ትሮሴል በጄኔቭ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፤ ከታህሳስ መጨረሻ ጀምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በተደረጉ የአየር ድብደባዎች ምክንያት የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ህይወት አልፏል ብለዋል፡፡
- መከላከያው ‘ወደ ትግራይ አይገባም’ መባሉን መቀበሏን አሜሪካ አስታወቀች
- “የተገኘው ድል ዘላቂ እንዲሆን በፖለቲካዊና ሰላማዊ መንገዶች እንዲቋጭ ይደረጋል”- ጠ/ሚ ዐቢይ
- መንግስት አቶ ስብሃት ነጋና አቶ ጃዋር መሃመድን ጨምሮ የተወሱ እስረኞችን በምህረት መልቀቁን አስታወቀ
የተፈጸመው የአየር ድብደባ በግለሰቦች ሚኒባስ፣ አውሮፕላን ማረፊያ እና የተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ ጣብያ ላይ እንደሆነም ተናግሯል፡፡
“ከሞቱት ሰዎች 59ኙ በሰሜን ምእራብ ትግራይ በሚገኘውና ደደቢት ተብሎ በሚታወቀው መጠለያ ጣብያ የነበሩ ተፈናቃዮች መሆናቸው ጥቃቱ እጅግ ገዳይ አድርጎታል”ም ነው ያሉት ቃል አቀባይዋ ሊዝ ትሮሴል ።
"በኢትዮጵያ አየር ሃይል ሳይፈጸም እንዳልቀረ በሚነገርለት የአየር ጥቃት ምክንያት ከጥር ወር ጀምሮ ቢያንስ 108 ንፁሀን ዜጎች ሲገደሉ 75 ሰዎች ቆስለዋል" ሲሉም አክሏል ሊዝ ትሮሴል።ተመድ ድርጊቱን ያወግዛል ያሉት ቃል አቀባይዋ ቢሯቸው እየወጡ ያሉት "በርካታ ዘገባዎች" እጅጉን እንደሚያሳስበውም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እና አጋሮቻቸው ኢላማዎች ወታደራዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ በሚጠይቀው አለም አቀፍ ህግ መሰረት የዜጎችን ደህንነት እንዲያረጋግጡ ሲሉም ጠይቋል።
ቃል አቀባይዋ "የልዩነት እና የተመጣጣኝነት መርሆዎችን አለማክበር የጦር ወንጀሎችን ሊያመለክት ይችላል"ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባለስልጣን በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ከፍተኛ ጦርነት ምክንያት በክልሉ የሚያከናውነውን ሰብዓዊ እርዳታ “ለማቆም እገደዳለው” ሲል አስጠንቅቋል፡፡የደብሊው ኤፍ ፒ ባልደረባ ቶምሰን ፒሪ “ምንም ምግብ፣ ነዳጅ ከሌለን፣ ተደራሽነት ከሌለን ለከባድ ሰብዓዊ አደጋ ልንጋለጥ ጫፍ ላይ ነን”ም ብሏል።
ህወሓት የፌደራል መንግስት በንጽሃን ላይ የአየር ጥቃት እያደረሰ ነው ሲል በተደጋጋሚ ክስ ያቀርባል፡፡ ነገርግን መንግስትም ኢላማው ወታደራዊ መሆኑንና ክሱን እንደማይቀበል በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ጥቅምት ወር 2013 የተጀመረው ጦርነት አንድ አመት ያለፈው ሲሆን በሺዎች እንዲገደሉና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል፡፡