የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሱዳን ባለስልጣናት የሥራ መልቀቂያ አስገቡ
የተደረሰው ስምምነት “የካቢኔ አባላት ወደ ስራቸው ይመለሳሉ ወይስ አይመለሱም?” ለሚለው በግልጽ ያለው ነገር የለም
ሚኒስትሮቹ መልቀቂያ ያስገቡት በሃምዶክ እና አል ቡርሃን መካከል የተደረገውን “የፖለቲካ ስምምነት” ተከትሎ ነው
አብደላ ሃምዶክ ወደ ሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲመለሱ ስምምነት ከተደረገ በኋላ 12 ሚኒስትሮች የሥራ መልቀቂያ መስገባታቸው ተሰማ፡፡
ሚኒስትሮቹ የሥራ መልቀቂያ ያስገቡት የሱዳን ጦር መሪ አብደል ፋታህ አልቡርሃን እና አብደላ ሃምዶክ ከሰሞኑ የስልጣን ክፍፍልን ማዕከል ያደረገ “የፖለቲካ ስምምነት” ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የሱዳን ሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በመፈንቅለ መንግስት ከኃላፊነታቸው ተነስተው የነበረ ቢሆንም በተደረገ ስምምነት ወደ ቦታቸው ተመልሰዋል፡፡
ሃምዶክ በስምምነቱ መሰረት ወደ ቦታቸው ቢመለሱም ግን፤ ስምምነቱን የካቢኔ አባላቱ የወደዱላቸው አይመስልም፡፡
አዲሱ የፖለቲካ ስምምነት ይፋ መደረጉን ተከትሎ 12 የሃምዶክ ሽግግር መንግስት ካቢኔ አባላት የሥራ መልቀቂያ አስገብተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት መርየም አል ሳዲቅ አል ማህዲ እና የመስኖ ሚኒስትር የነበሩት ፕሮፌሰር ያሲር አባስን ጨምሮ የፍትህ፣ የግብርና፣ የኢንቨስትመንትና የኃይል ሚኒስትሮች የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውም ነው የተሰማው፡፡
ከዚህም በተጨማሪም የትምህርት፣ የስራ፣ የትራንስፖርት፣ የጤና፣ የወጣቶችና የኃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትሮችም የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸው ይፋ ሆኗል፡፡
“ሱዳን ከግልበጣው ጀምሮ በእስር ላይ ነው ያለችው”- መርየም አል ሳዲቅ፣ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩ
የሱዳን ሉዓላዊ ሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በሀገሪቱ ጦር መፈንቅለ መንግስት ከተፈፀመ ሶስት ሳምንታት በኋላ ስልጣን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ የሚያስችል ስምምነት ከአንድ ቀን በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ጋር መፈራረማቸው አይዘነጋም፡፡
የሲቪል አስተዳደሩ ወደ ቦታው ይመለስ እንጂ የሃምዶክ ካቢኔ አባላት ግን እስካሁን ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ውሳኔ እሰካሁን አልተላለፈም፡፡
በሱዳን የተደረገው መፈንቅለ መንግስት፤ ከሀገሪቱ አልፎ የቀጠናውን ሰላም ያናጋል በሚል በዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አብደል ፈታህ አልቡርሃን የሲቪል አስተዳደሩን በመፈንቅለ መንግስት ማንሳታቸው ከፍተኛ ውግዘት አስከትሎባቸው ነበር፡፡
ተመድ፣ አፍሪካ ህብረት፣ የአውሮፓ ሕብረት እና አሜሪካም በሱዳን ተደርጎ በነበረ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የተነሱት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና የካቢኔ አባላት ወደ ኃላፊነታቸው እንዲመለሱ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡