“ነገሮች ሲሻሻሉ በደሴ እና ኮምቦልቻ የተቋጠው ድጋፍ ይቀጥላል”- ተመድ
በጦርነቱ ከተጎዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች መካከል ቢያንስ 400 ሺ ያህሉ ለከፋ የምግብ ችግር መጋለጣቸውን ተመድ ይፋ አድርጓል
“ህወሓት ዜጎችን አምስት ጊዜ አፈናቅሏል”- መንግስት
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአማራ ክልል በሚገኙ መጋዘኖቹ መዘረፍ ምክንያት በደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች ያቋረጠውን እርዳታ ነገሮች ሲሻሻሉ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡
የተመድ የኢትዮጵያ ቢሮ ማስተባበሪያ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ በሰጠው መግለጫ በኮምቦልቻ እና ደሴ ከተሞች የነበሩት መጋዘኖች “በትግራይ ኃይሎች” መዘረፉን ገልጿል፡፡
የቢሮው እና የተመድ ሰብዓዊ ድጋፍ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ኃላፊ ዶ/ር ካትሪን ሶዚ በሁለቱ ከተሞች ያለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን በህወሃት መዘረፉን አረጋግጠዋል።
የተመድ ሰራተኞች በዛቻ እና ማስፈራሪያ እንዲሁም ጠብመንጃ እየተደቀነባቸው ስለነበር የመጋዘኖቹን ዝርፊያ ማስቆም አለመቻላቸውን ዶ/ር ካትሪን አስታውቀዋል፡፡
ለትግራይ ክልል ቶሎ ቶሎ እርዳታ እንዲደርስ ደጋግሞ የሚያሳስበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት “የአፋር እና የአማራ ክልሎችን ዘንግቷል” በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ፤ ተመድ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩል ዐይን እንደሚመለከት አንስተዋል ዶ/ር ካትሪን፡፡
በኢትዮጵያ ከእርዳታ ስርጭት ጋር በተያያዘ “ምንም አይነት መድልዎ” አይፈፀምም- የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን
ጦርነቱ በአማራ ክልል 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን፣ በአፋር ክልል ከ500 ሺ በላይ እንዲሁም በትግራይ ክልል 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎችን መጉዳቱን ገልጸው ከዚህ ውስጥ ቢያንስ 400 ሺ የሚሆኑት ለከፋ የምግብ ችግር መጋለጣቸውንም ነው ይፋ ያደረጉት፡፡
መንግስት በአፋርና በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎችን እየደገፈ ነው ያሉት የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በበኩላቸው እርዳታ ሰጭ ተቋማት “የለጋሾቻቸውን ፍላጎት ብቻ ነው” ሲሉ ተችተዋል፡፡
ኮሚሽነር ምትኩ “በህወሓት ምክንያት አምስት ጊዜ የተፈናቀሉ ዜጎች አሉ” ያሉ ሲሆን ቡድኑ ዜጎችን ከአላማጣ እስከ ደብረብርሃን ማፈናቀሉን ተናግረዋል፡፡
በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት እርዳታን እንደጦር መሳሪያ መጠቀሙን ገልጸዋል ኮሚሽነር ምትኩ፡፡
ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ ነው-መንግስት
በሰሜን ወሎ ቀደም ሲል ጀምሮ በሴፍትኔት ይተዳደሩ የነበሩ ዜጎች አምስት ወራት ሙሉ እርዳታ እንዳላገኙ ለአብነት በማንሳትም ዜጎቹ ድጋፍ እንዲያገኙ ብዙ ጥረት ቢደረግም እንዳልተቻለና አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንደማይታወቅ ገልጸዋል፡፡ በዋግ ኸምራ ዞንም ተመሳሳይ ሁኔታ እንደገጠመም ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት፡፡
እርዳታ ሰጭዎች በጥቅሉ አፋር እና አማራ ክልሎችን መዘንጋታቸውን ጠቅሰው የሴፍቲኔት እና የእርዳታ አቅርቦት የተቋረጠባቸው፤ የተዘረፉ እንዲሁም የተፈናቀሉት ዜጎች በጥቅሉ 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን መሆናቸውንም አስቀምጠዋል፤ ህወሓት “ከጨው ጀምሮ እስከ ማሳ ላይ ያለ ሰብል” መዝረፉን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፡፡
በአማራ ክልል ሞጣ፣ እብናት፣ ደብረብርሃን፣ ደባርቅ፣ መካነ ሰላም ከተሞች የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ልብስ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን መቀባቸውንም ገልጿል ተመድ፡፡
በአምደወርቅ፣ በንፋስ መውጫ እና መቄት ያሉ ሆስፒታሎች እንዲሁም በዋግ ኸምራ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር እና ሰሜን ወሎ የሚገኙ የጤና ተቋማት ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ የጤና አጋሮች ማገዛቸውን አስተባባሪዋ ገልጸዋል፡፡
በአፋር እና በአማራ ክልል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አጋሮች ድጋፋቸውን እያጠናከሩ መሆኑን የገለጹት የተመድ የኢትዮጵያ አስተባባሪ ድጋፍ ሰጭዎችም የጸጥታው ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው በመጥቀስ 23 ሰብዓዊ ሰራተኞች ህይወታቸውን ማጣታቸውንም ለአብነትም አንስተዋል፡፡
በእርዳታ ማከማቻ መጋዘኖቹ መዘረፍ ምክንያት በደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች የሚያደርገውን የምግብ ድጋፍ ማቆሙን የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዛሬ ጠዋት መግለጹ ይታወሳል፡፡