“ኢትዮጵያ የቀሩ ወገኖቻችን ይምጥሉን” ያሉ ቤተ እስራኤላውያን ዛሬ በእየሩሳሌም ሰልፍ አደረጉ
ቤተ እስራኤላውያኑ የእስራኤል ካቢኔ በሚሰበሰብበት በዛሬው ዕለት ነው ሰልፉን ያደረጉት
ወገኖቻችን ችግር ላይ ይገኛሉ ያሉት ሰልፈኞቹ የሃገራቸው መንግስት በአስቸኳይ እንዲያመጣላቸው ጠይቀዋል
ቤተ እስራኤላውያን በኢትዮጵያ የቀሩ ወገኖቻችን በአስቸኳይ ሊመጡ ይገባል በሚል በእየሩሳሌም ሰልፍ አደረጉ፡፡
“ወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ አሳስቦናል ወገኖቻችንም ችግር ላይ ይገኛሉ፤ እየታሰሩ እየተገደሉም ነው” ያሉት ቤተ እስራኤላውያኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ጽህፈት ቤት አካባቢ መሰለፋቸው የተለያዩ የእስራኤል ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡
ቤተ እስራኤላውያኑ የዛሬውን የእስራኤል ካቢኔ ስብሰባ ታሳቢ አድርገው ድምጻቸውን ለማሰማት መሰለፋቸውም ነው የተነገረው፡፡
እስራኤል በዚህ ዓመት መጨረሻ 4,500 ፈላሻዎችን ከኢትዮጵያ እወስዳለሁ አለች
ካቢኔው ጉዳያችንን ጉዳዩ እንዲያደርገው እና በጀትን ጨምሮ አስፈላጊውን ውሳኔ እንዲያሳልፍ ለመጠየቅ ነው የተሰለፍነውም ብለዋል ሰልፈኞቹ ሰልፉን በማስመልከት በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲተላለፉ በነበሩ የቀጥታ የቪዲዮ ስርጭቶች፡፡
ስፋት ከተባለ የመጠለያ ስፍራ ነው የመጣሁት ያሉ አንድ ሰልፈኛ ወገኖቻችንን ለማምጣት በመንግስት በተወሰነው መሰረት በአስቸኳይ እንዲመጡ መንግስትን ለመጠየቅ ነው የመጣነው ብለዋል፡፡
ሰልፈኞቹ ወደ እስራኤል እንዲመጡ የተፈቀደላቸው ቤተ እስራኤላውያን ጉዳይ በሃገሪቱ መንግስት ችላ መባሉ እንዳስቆጣቸውም ነው ያስታወቁት፡፡
የእስራኤል የኢሚግሬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት ቤተ እስራኤላዊቷ ፕኒና ታመነ እሸቴ ወደ ካቢኔ ስብሰባው ከመግባታቸው በፊት ሰልፈኞቹን አናግረዋል፡፡
በንግግሩ በሁኔታው ማዘናቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ አሁንም የሃገራቸው መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ለማድረግ መታገላቸውን እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል፡፡
እስራኤል በፕኒና አስተባባሪነት በ‘ሮክ ኦፍ እስራኤል’ ዘመቻ እስካሳለፍነው ጥር ድረስ 2 ሺ ቤተ እስራኤላውያንን ለመውሰድ አቅዳ ስትሰራ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከቤተ እስራኤላውያኑ ጋር በተያያዘ በሚያነሷቸው የመብትና የፖለቲካ ጥያቄዎች የሚታወቁት ዶ/ር አቭርሃም ንጉሴም በሰልፉ ንግግር አድርገዋል፡፡
ዶ/ር አቭርሃም በንግግራቸው “ጥያቄያችን በምንም ዐይነት መልኩ ከጦርነቱ ጋር የሚገናኝ፤ አሸናፊ ተሸናፊ አለ በሚል የሚደረግም አይደለም” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ከሰሞኑ ‘ካአን ሬካ’ ከተባለ ሬዲዮ የአማርኛ ዝግጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አቶ አለልኝ አድማሱ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የአካባቢያቸውን ሰላም በጋራ እየጠበቁ እንደሆነና በተለየ የደረሰባቸው ችግር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
ከተለያዩ የኢትዮጵያ መንግስት አካላት ጋር ተገናኝተው መምከራቸውን የተናገሩት አምባሳደር አለልኝ የሃገራቱ ግንኙነት ጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን እና የበለጠ ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በኩል ጦርነት ቢኖርምና ጥንቃቄ ቢያስፈልግም በውጭ አካላት እንደሚነገረው በኢትዮጵያ የተለየ ችግር እንደሌለም ነው “ማየት ማመን ነው” ያሉት አምባሳደሩ የተናገሩት፡፡
ከሰሞኑ ወደ እስራኤል ለመሄድ በመጠባበቅ ላይ ናቸው የተባሉ 5 ሺህ ቤተ እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ለመውሰድ የእስራኤል መንግስት ወስኗል በሚል ሲወራ ነበር፡፡