በኮፕ28 እስካሁን የተደረሱ ስምምነቶች ምንድን ናቸው?
ከ83 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ቃል የተገባበት ጉባኤ ከ11 በላይ የስምምነት ሰነዶች ተፈርመውበታል
የግብርና እና ምግብ ስርአቱን ለማዘመን የሚያግዙ ስምምነቶችም ተደርሰዋል
12ኛ ቀኑን የያዘው ኮፕ28 በርካታ ስምምነቶች የተደረሱበት የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ሆኗል።
በጉባኤው በጤና፣ በግብርና፣ በምግብ ስርአት እንዲሁም በታዳሽ ሃይል ልማት ከ11 በላይ የቃልኪዳን ሰነዶች ተፈርመውበታል።
በጉባኤው የመጀመሪያ ቀን ውሎ የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድን ስራ ለማስጀመር ከስምምነት ተደርሷል።
ሀገራት በዱባዩ ጉባኤ ለአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ 792 ሚሊየን ዶላር ለማዋጣትም ቃል መግባታቸውም የሚታወስ ነው።
3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያለው የ”ግሪን ክላይሜት ፈንድ” ለማቋቋምም ቃል ተገብቷል።
በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ ለሚጎዱ ሀገራት የሚደረገው ድጋፍ እንዲያድግና ለሚደርስባቸው ጉዳትና ኪሳራ ዋነኞቹ በካይ ሀገራት በሚያዋጡት ገንዘብ ዙሪያም ሰፊ ምክክር ተደርጎ ከስምምነት ተደርሷል።
የጉባኤው አዘጋጅ ኤምሬትስም “አልቴራ” የሚል ስያሜ ያተሰጠውን የ30 ቢሊየን ዶላር የአየር ንብረት ለውጥ ኢንቨስትመንት ፈንድ ማስተዋወቋ አይዘነጋም።
በኮፕ28 ጉባኤ የአለም ባንክም የአየር ንብረት ለውጥን ለሚቀንሱ ስራዎች የሚያቀርበውን ብድር በ2024 እና 2025 ወደ 9 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል።
ሌሎች አለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማትም የአየር ንብረት ለውጥን ለሚቀንሱ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጨማሪ 22 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ለማቅረብ ከስምምነት ደርሰዋል።
የታዳሽ ሃይል ልማትን ለማስፋፋት በስፋት የተመከረበት የዱባዩ ጉባኤ፥ 130 ሀገራት የታዳሽ ሃይል ልማታቸውን በሶስት እጥፍ ለማሳደግ የተስማሙበት ሆኗል።
153 ሀገራትም “የምግብ ስርአት፣ ዘላቂ ግብርና እና አየር ንብረት ለውጥ ዲክላሬሽን”ን ፈርመዋል።
ከማቀዝቀዣ ቁሳቁሶች የሚለቀቅ በካይ ጋዝን በ2030 በ68 በመቶ ለመቀነስ የሚያስችል ስምምነትም በ66 ሀገራት መካከል ተፈርሟል።
የአለማችን 40 በመቶ ብክለት የሚያስከትሉ 52 የነዳጅና ጋዝ ኩባንያዎች የካርበን ልቀታቸውን ለመቀነስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈረረሙት ሰነድም የኮፕ28 ጉባኤን ታሪካዊ ካሰኙት ስምምነቶች ተጠቃሽ ነው።
በጉባኤው ሀገራት እና ኩባንያዎች ለተለያዩ የአየር ንብረት ለውጥ ጥበቃ ስራዎች እና ለተጎጂዎች ድጋፍ ለማድረግ ከ83 ቢሊየን ዶላር ለመለገስ ቃል መግባታቸውም የጉባኤው ሌላኛው ስኬት ሆኗል።
ጉባኤው በነገው እለት ሲጠናቀቅ የሚፈረመው የኮፕ28 የስምምነት ሰነድም ምድራችን በአሁኑ ወቅት ለምትፈተንበት የአየር ንብረት ለውጥ ዘላቂ መፍትሄዎች ይመላከታሉ ተብሎ ይጠበቃል።