የሽግግር ጊዜ ፍትሕ በኢትዮጵያ አሁናዊ ተጨባጭ ሁኔታ እንዴት ሊሳካ ይችላል?
የሽግግር ጊዜ ፍትሕ በመደበኛው የፍትህ ስርዓት ሊዳኙ የማይችሉ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ የሚተገበር የፍትህ ሂደት ነው- ምሁራን

ጥቂት ጥፋተኞችን በወንጀል አስቀጥቶ ከሚገኘው “ያለፈ ፍትህ” የሚፈለግበት የሽግግር ጊዜ ፍትሕ “ከከሳሽ እና ተከሳሽ ማዕቀፍ” እንደሚሰፋም ምሁራን ይናገራሉ
የሽግግር ጊዜ ፍትህ ጉዳይ በድጋሚ እንደ አዲስ እየተቀነቀነ ይገኛል፡፡ ጽንሰ ሃሳቡ ከአሁን ቀደም በተለያዩ ጊዜያት የተነሳ ቢሆንም ሃገራዊ ለውጥ እንደተደረገ ከተነገረበት ከ2010 ዓ/ም ማግስት ጀምሮ ብዙ ሲባልበት ነበረ፡፡
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመራው የለውጥ መንግስት ለለውጥና ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንደሚተጋ መግለጹን ተከትሎ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በጽንሰ ሃሳቡ ዙሪያ እና በአተገባበሩ ላይ ምሁራዊ ምክክሮች ሲደረጉ እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
በቅርቡ ለታሰበው ሃገራዊ ምክክር ይበጃል በሚል የተወሰኑ እስረኞች ክሳቸው ተቋርጦ ሲፈቱ የሽግግር ፍትሕ ጉዳይ መነሳቱ ይታወሳል፡፡
የተጎጂዎች ቁስል በሽግግር ፍትሕ እንደሚካስ መንግስት ማስታወቁም አይዘነጋም፡፡ ሆኖም በእንዲህ አይነት መንገድ የሽግግር ጊዜ ፍትህን ለማረጋገጥና ሃገራዊ እርቅና መግባባትን ለማሳካት ይቻላል ወይ በሚል የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛም ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት የህግ ባለሙያዎችንና ምሁራንን ጠይቋል፡፡
የሽግግር ጊዜ ፍትህ “ጥቂት ጥፋተኞችን በወንጀል አስቀጥቶ ከሚገኘው ያለፈ ፍትህ” ይገኛል ተብሎ የሚታሰብበት ስርዓት ነው የሚሉት የህግ ባለሙያው አምሃ መኮንን ቀድሞ ከነበረ አንድ ስርዓት ወደሚታሰብ ሌላ አዲስ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚደረግ ሽግግር ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡
በዚህ ሽግግር ውስጥ የሚታዩ የከፉ የመብት ጥሰቶች እንዴት ይዳኙ የሚለው ምላሽ በሽግግር ፍትህ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
አቶ አምሃ የሽግግር ጊዜ ፍትሕ በመደበኛው የፍትህ ስርዓት ሊዳኙ የማይችሉ ጉዳዮች ሲያጋጥሙና በመቶዎች ወይም በሺዎች የሚቆጠሩ ጥፋተኞች ሲኖሩ እንደየጥፋት ደረጃቸው ተጠያቂ ለማድረግ ይቅር የሚባለውን ይቅር ለማለት የሚተገበር መሆኑንም ያነሳሉ፡፡
የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብትም ይሁኑ ሌሎች ጥሰቶች ከመክፋታቸውም በላይ መስፋታቸውን ተከትሎ አሁንም የሽግግር ጊዜ ፍትሕ ጉዳይ በድጋሚ ሊቀነቀን መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህሩ ደመላሽ ሽፈራው (ዶ/ር)ም የሽግግር ፍትህ ምንነት ከዚሁ የሚመነጭ መሆኑን ያነሳሉ፡፡
ከህወሓት ጋር በመደረግ ላይ ያለውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት ከበድ ያሉ የተለያዩ ጥሰቶች ሲፈጸሙ ነበር፡፡ በጥሰቶቹ ለህልፈተ ህይወት ከተዳረጉት ባሻገር ለተለያዩ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳቶች የተዳረጉ ጥቂት አይደሉም፡፡ ልክ እንደተጎጂዎቹ ሁሉ የጥሰቶቹ ዓይነትና ፈጻሚዎቹም ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህን በሙሉ የወንጀል ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም፤ የፍትህ ስርዓቱ ራሱ አይችለውም እንደሚሉት እንደ ዶ/ር ደመላሽ ገለጻ፡፡
በመሆኑም የሚፈለገውን ፍትህ ጨምሮ ቂምና ቁርሾዎችን በእርቅና በተለያዩ መንገዶች ለማስቀረት ከመደበኛው የዳኝነት ስርዓት የተሻገረ የሽግግር ጊዜ ፍትህን ማስፈን ያስፈልጋል፡፡
ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን መቋቁሙንም የህግ መምህሩ ያስታውሳሉ፤ ምንም እንኳን ኮሚሽኑ የተጠበቀውን ያህል ሚና ለመጫወት ባይችልም፡፡
የሽግግር ጊዜ ፍትህ “በለውጥ ማዕቀፍ ውስጥ ነው ሊታሰብ የሚችለው” የሚሉት ስማቸውን ለመግለጽ ያልፈለጉ አንድ የህግ መምህር በበኩላቸው ሁሉም በእኩልነት ሊጠየቅ የሚችልበት ነገር ግን ደግሞ አልፎ ተሻግሮ ወደ ሌላ አዲስ ምዕራፍ የሚገባበት ነው ይላሉ፡፡
ሆኖም መሰረታዊ ለውጥን ታሳቢ አድርጎ ያለፈውን ስርዓት ችግሮች በተወሰነ መልኩ ምላሽ የሚሰጥበት እንጂ ዝም ብሎ ሂሳብ የማወራረድ ነገር እንዳይደለ ያስቀምጣሉ፡፡
ሃገርን ለመጠበቅ፣ ለመታደግና ለማዝለቅ በማሰብ የሚደረጉ የይቅርታና የእርቅ ሂደቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ በማስታወስም ይህ ግን ሊሆን የሚችለው “የተለወጠ ስርዓት ባለበት ሁኔታ ውስጥ ነው” ይላሉ፡፡
ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አሁናዊ ተጨባጭ ሁኔታ ያንን ለማስተናገድ የሚፈቅድ አይደለም እንደ ህግ ምሁሩ ገለጻ፡፡
የሽግግር ጊዜ ፍትህ አስፈላጊ ቢሆንም “ከስም የዘለለ ተጨባጭ ለውጥ የሚገኝበት ነው ብዬ አላስብም” ም ብለዋል፡፡
ጦርነቱ ባልተቋጨበት ሁኔታ የሽግግር ጊዜ ፍትህን ለማስፈን ይቻላል ወይ ሲሉ ብዙዎች ያጠይቃሉ፡፡ በሽግግር ፍትህ ስም የተበዳዮች የፍትህ ጥያቄ ተድበስብሶ ሊቀርና ወንጀለኞችም ተገቢውን ቅጣት ሳያገኙ ሊቀሩ እንደሚችሉ የሚሰጉም ጥቂት አይደሉም፡፡
የሽግግር ፍትህ “የግጭት መፍቻ አካል ነው” የሚሉት ዶ/ር ደመላሽ ግጭቱ ባልተቋጨበት ሁኔታ ሊታይም እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡ ይህ ግን በግልጽ ተለይቶ የተቀመጠ ዓላማን ይፈልጋል፡፡ ከዚህ አንጻር የተፈጸሙ በደሎችን መርምሮ አጣርቶ እውነቱን ማሳወቅ በራሱ አንዱ የፍትህ አካል ሊሆን ይችላል እንደ ምሁሩ ገለጻ፡፡
ሆኖም ይህ ሲሆን የወንጀል ተጠያቂነት ሰፍኖ ነው፡፡ ከሽግግር ፍትሑ ጎን ለጎን በተለይ በህገ መንግስቱ ይቅርታና ምህረትን የማያሰጡ ከባድ ወንጀለኞችን ተጠያቂ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ይህን በማረጋገጥ የተበዳዮችን ጥያቄ ከመመለስም በላይ በማህበረሰቡ ውስጥ በሂደት እርቅ ሊያመጡ የሚችሉ የገንዘብና የሌሎች የዐይነት ካሳዎች ሊደረጉም ይችላሉ፡፡
ስማቸውን ለመግለጽ ያልፈለጉት ምሁርም “ከከሳሽ እና ተከሳሽ ማዕቀፍ የሚሰፋ ነው” በሚሉት የሽግግር ፍትህ ውስጥ የከፋ ጉዳት የደረሰበትን የማህበረሰብ ክፍል በተለያዩ የማህበራዊ የማከሚያ መንገዶች በልማት መካስ እንደሚቻል ያስቀምጣሉ፡፡