የአንቶኒዮ ብሊንከን የአፍሪካ ጉዞ ተጀምሯል
ብሊንከን፤ ከትናንት በስቲያ እሁድ ኢትዮጵያ ከነበሩት የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ይመክራሉ ተብሏል
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኬንያን ጨምሮ ናይጄሪያ እና ሴኔጋልን ይጎበኛሉ
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የአፍሪካ ጉብኝት ጉዞ ተጀምሯል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ እስከ ፈረንጆቹ ህዳር 20 ድረስ በተለያዩ ሶስት የአፍሪካ ሃገራት ጉብኝት የሚያደርጉት ብሊንከን የ5 ቀናት ጉብኝታቸውን ዛሬ ጀምረዋል፡፡ ብሊንከን ወደ ጎረቤት ሃገር ኬንያ፣ ናይጄሪያ እና ሴኔጋል ነው የሚጓዙት፡፡
የዛሬ ጉዟቸው ወደ ኬንያ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ጉዞ መጀመሩን ያስታወቀው ቃል አቀባያቸው ኔድ ፕራይስ በምጣኔ ሃብታዊ፣ በአየር ንብረት እና በዴሞክራሲያዊ እንዲሁም በጸጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ከሚጎበኗቸው ሃገራት መሪዎች ጋር ይወያያሉ ብሏል፡፡
“ኮ/ል መንግስቱ ከሀገር የወጡበት ጉዳይ ቢጠና የማጭበርበር ውጤት አካል እንደሚሆን ጥርጣሬ የለኝም”- ጠ/ሚ ዐቢይ
በናይሮቢ በሚኖራቸው ቆይታ ከኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በሁለትዮሽና በሌሎች ቀጣናዊ ጉዳዮች በዋናነትም በኢትዮጵያ ወቅታዊ የጸጥታ ደህንነት ሁኔታዎች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከትናንት በስቲያ እሁድ ህዳር 5 ቀን 2014 ዓ/ም ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ሌሎች የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተዋል፡፡
ኬንያታ የብሊንከን የአፍሪካ ጉዞ ከመጀመሩ ከቀናት በፊት ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፡፡
ኡሁሩ ኬንያታ፤ ብሊንከን ናይሮቢ ከመግባታቸው ከአንድ ቀን በፊት ለምን አዲስ አበባ መጡ?
የፕሬዝዳንቱ የአንድ ቀን ጉብኝት ምናልባትም በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ህወሓት ጋር በተያያዘ በአሜሪካና በአጋሮቿ በኩል ለኢትዮጵያ መንግስት በሚቀርቡ የተደራደሩ ጥያቄዎች ዙሪያ ለመምከር እና ሁኔታዎችን ለመፈተሸ ሊሆን ይችላል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከአሁን ቀደም፤ በተለይም ወደ አሜሪካ አቅንተው በዋሽንግተን ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ተወያይተው ከተመለሱ በኋላ የኢትዮጵያ ተፋላሚ ወገኖች ተኩስ አቁመው ወደ ድርድር እንዲመጡ ሲያሳስቡ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አሜሪካ ከፕሬዝዳንት ባይደን ወደ ስልጣን መምጣት ወዲህ ኬንያን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሁነኛ አጋር አድርጋ መቁጠር ጀምራለች፡፡
ዋሽንግተን ለናይሮቢ ልትሰጥ ከምታስበው ከዚህ የቀጣናዊ የአጋርነት ሚና ጋር በተያያዘም ሊሆን ይችላል ኬንያታ ወደ አዲስ አበባ የመጡት፡፡
ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች አፍሪካዊ ጉዳዮች በአፍሪካውያን መፍትሄ ይፈለግላቸው የሚል አቋም እንዳላትም ይታወቃል፡፡
“በኢትዮጵያ ግጭት ተዋንያን መካከል ያለው ዋና ልዩነት፤ ‘የሰላም መንገዱ ምን ይሁን’ የሚል ነው”- ኦባሳንጆ
ብሊንከንም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከፕሬዝዳንት ኬንያታ ጋር ከመሩ በኋላ ወደ ናይጄሪያ አቅንተው ከፕሬዝዳንት መሃመዱ ቡሃሪ እና ሌሎች የሃገሪቱ ባለስልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡
አሜሪካ፤ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት የሰላም ጥረት እውቅና እንደምትሰጥና እንደምትደግፍ ማስታወቋ የሚታወስ ነው፡፡
ኦባሳንጆ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ መሆናቸውም ይታወቃል፡፡
አዛውንቱን ኦባሳንጆ ጨምሮ ፕሬዝዳንት መሃመዱ ቡሃሪ እና ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች ትናንት ደቡብ አፍሪካ ነበሩ፤ በአህጉራዊው የንግድ ትርዒት (IATF) መክፈቻ ላይ ለመሳተፍ፡፡
የብሊንከን የአፍሪካ ጉዞ ወደ ሴኔጋል በማቅናት ነው የሚጠናቀቀው፡፡ በሴኔጋል ከመጪው ዓመት የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ከፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ጋር ይወያያሉ፡፡
ይህ የብሊንከን የአፍሪካ ጉዞ ምናልባትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመራውን የኢትዮጵያ መንግስት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀርቡ አፍሪካውያን ወዳጆች በኩል ለማግባባት በማሰብ የሚደረግ ሊሆን ይችላል፡፡
የሶስቱም የአፍሪካ ሃገራ መሪዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዓለ ሲመት ላይ መገኘታቸው አይዘነጋም፡፡