ሊጠናቀቅ የቀናት እድሜ ብቻ በቀረው 2021 ምርጫ እና ጦርነትን ጨምሮ በርካታ ፖለቲካዊ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች በኢትዮጵያ አጋጥመዋል
ኢትዮጵያ ሊጠናቀቅ በተቃረበውና የቀናት እድሜ ብቻ በቀረው የፈረንጆቹ 2021 ዓመት ዐይነተ ብዙ ጉዳዮችን አስተናግዳለች፡፡ ጉዳዮቹ ይበልጥ ተጋግሎ ለጦርነት መነሻ ከሆነው ፖለቲካዊ ውጥረት አንስቶ ሌሎች ኃያል ነን ባይ የውጭ ሃገራትን እስከጋበዘው ዲፕሎማሲዊ ትንቅንቅና እሰጣገባ፤ ብዙዎችን በልቶ ከማደር ስር ወደሰደደ የድህነት አረንቋ እስከመክተት እስካደረሱ ዐይን ያፈጠጡ ምጣኔ ሃብታዊ ተግዳሮቶች እና ሻጥሮች የሚዘረጉ ናቸው፡፡
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ የድርድር እና የሙሌት ሂደቶች እንዲሁ ሲያነጋግሩ መክረማቸውም የሚታወስ ነው፡፡
በነዚህ ገመድ ጉተታ መልክ በነበራቸው ፖለቲካ ቀመስ የአውራነት ትንቅንቆች ምክንያት በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ለዓመታት በፈሰሰ ላብ የተገነባ ሃብታቸውን አጥተዋል፤ ተወልደው ካደጉበት ቀዬ ተፈናቅለውም ለከፋ እንግልትና ስቃይ ተዳርገዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛም እነዚህኑ ጉዳዮች ከግምት ውስጥ በማስገባት ሊጠናቀቅ በተቃረበው የፈረንጆቹ ዓመት በኢትዮጵያ ያጋጠሙ አንኳር አነጋጋሪ ሃገራዊ ጉዳዮችን በተከታዩ መንገድ አጠናቅሯል፡፡
ጦርነት…አጀማመሩ እና አሁናዊ ሁኔታው
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ/ም በትግራይ ክልል ይገኝ በነበረው ሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመውን “ዘግናኝና ድንገተኛ የክህደት ጥቃት”ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ዓመቱን ሙሉ ሲያነጋግሩ እና ህዝብ ዐይኑን ሳይነቅል ሲከታተላቸው ከነበሩ ቀዳሚ አንኳር ሃገራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱና ቀዳሚው ነው፡፡ “መብረቃዊ” በሚል በራሱ በህወሓት አመራሮች የተገለጸውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነቱ 14 ገደማ ወራትን አስቆጥሯል፡፡ በጥቃቱ የተቆጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን መከላከያውን ደግፈው ወደ አደባባዮች መውጣታቸው ይታወሳል፡፡
በነዚህ የጦርነት ወራት ውስጥ ዐይነተ ብዙ የጦር ሜዳ ሁነቶች ተስተውለዋል፤ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቶች ደርሰዋል፡፡
ጥቃቱን ተከትሎ መንግስት “ህግ ለማስከበር” በሚል የጀመረው ዘመቻ በአጭር ቀናት መጠናቀቁ ቢነገርም ቅሉ የኋላ ኋላ አጋሩ ነው ከተባለው ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጋር በሽብርተኝነት የተፈረጀው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ተዋጊዎች “እንደ አቧራ ተበትነዋል” ከባሉበት የተምቤን በረሃዎች ወጥተው ከክልላቸው አልፈው አብዛኛዎቹን የአማራ ክልል አካባቢዎች በወረራ ለማዳረስ ችለዋል፡፡
ይህ ለዘመቻው ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ማውጣቱን የገለጸው የፌዴራሉ መንግስት የጥሞና ጊዜ ያስፈልጋል በሚል የወሰደውን የተናጠል ተኩስ አቅም እርምጃ ተከትሎ የሆነ ነው፡፡
በዚህም ይህ ነው የማይባል እጅግ አስከፊ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት መድረሱ ተነግሯል፡፡ በርካቶች ተገድለዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ለተለያዩ ጾታዊ ጥቃቶች ተዳርገዋል፤ የጤና እና የትምህርትን ጨምሮ መሰረተልማቶችም ወድመዋል፡፡
እስከ ሰሜን ሸዋ ቆላማ እና ደጋማ አካባቢዎች በመድረስም “አዲስ አበባን ለመቆጣጠር የቀናት እድሜ ብቻ ይቀረናል” እስከማለት ደርሰው እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
ተከታታይ ህዝባዊ የክተት ጥሪዎች በአማራ ክልል በፌዴራል መንግስትም ደረጃ ተደርገው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ሆኖም ከሰኔ 21 ቀን 2013 ጀምሮ ያወጀው የተናጠል ተኩስ አቁም አለመስራቱን የተመለከተው መንግስት ዘግይቶም ቢሆን የተጠናከሩ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻዎች ለማድረግ ተገዷል፡፡
በዘመቻዎቹ የተሳኩ ድሎችን ማስመዝገቡን በሰበር ባሳወቃቸው ተከታታይ መግለጫዎች ይፋ አድርጓል፡፡ እስከ ከፊል ሰሜን ሸዋ ዘልቀው ለመግባት ችለው የነበሩት የህወሓት ተዋጊዎች አፋርን ጨምሮ በወረራ ይዘዋቸው ከነበሩ የምስራቅ አማራ አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውንም ነው መንግስት ያስታወቀው፡፡
ለዚህ የአማራ እና የአፋር ልዩ ኃይል እና ሚሊሻዎችን ጨምሮ የፋኖ አበርክቶ የጎላ ነው፡፡ መላው ኢትዮጵያውያንም አቅም በፈቀደ መጠን ተረባርበዋል፤ ምንም እንኳን ህወሓት ተሸንፈው ሳይሆን በስልታዊ ማፈግፈግ እንጂ ተሸንፎ የገባባቸውን አካባቢዎች እንዳልለቀቀ ቢገልጽም፡፡
“ከአሁን ቀደም ካጋጠሙ ችግሮች መማር ይገባል” ያለው መንግስትም ጦሩ ወደ ትግራይ ክልል ከመግባት ይልቅ ነጻ ባወጣቸው የአፋር እና የምስራቅ አማራ አካባቢዎች ጸንቶ እንደሚቆይ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ የሚያሠጋ ነገር ካጋጠመ ሰራዊቱ በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ወደ ትግራይ ክልል ይገባል- ጠ/ሚ ዐቢይ
የዚህ ጦርነት ጉዳይ በህዳሴው ግድብ የግንባታ ሂደት እና በሁለተኛ ዙር ሙሌት ምክንያት ደስታ ላይ የነበሩትን ኢትዮጵያውያንን ሲያነጋግሩ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የህዳሴ ግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት
“ድህነትን መሻገሪያዬ ነው” በሚል ኢትዮጵያ በራሷ አቅም በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግብድ ሁለተኛ ዙር ሙሌት የተፈጸመው በዚሁ ባጠናቀቅነው የፈረንጆቹ ዓመት 2021 ወርሃ ሃምሌ ላይ ነበር፡፡
በወቅቱ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ነበሩት ኢ/ር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) “ዛሬ ሀምሌ 12 ቀን 2013 ዓ/ም የሁለተኛውን አመት የህዳሴ ግድብ ሙሌት ተገባዶ ውሃው በግድቡ አናት ላይ ፈሶአል፤ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንኩዋን ደስ አላችሁ” ሲሉ የደስታ መግለጫቸውን በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ማጋራታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ሃምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም በተጠናቀቀው የመጀመሪያ ዙር የግድቡ ሙሌት 4.9 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ የያዘችው ኢትዮጵያ በሁለተኛው ዙር ሙሌት ከ13 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ በላይ ውሃን ለመያዝ ችላለች፡፡
ይህ ግንባታው ከ80 በመቶ በላይ የተጠናቀቀው ግድብ ሁለት ተርባይኖች ኃይል እንዲያመነጩ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ተርባይኖቹ በነሃሴ መጨረሻ 700 ሜጋ ዋት ኃይልን ማመንጨት ይጀምራሉ ተብሎ እንደነበርም ይታወሳል ምንም እንኳን ያ ሳይሆን ቢቀርም፡፡
ግድብ አሁን ባለው የግንባታ ቁመት 400 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል-የግድቡ ተደራረዳሪ
የግድቡ 2ኛ ዙር ሙሌት ወቅቱን ጠብቆ ቢካሄድም በተለያዩ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፏል፡፡
ወትሮውኑ የግድቡን መገንባት በስጋትነት ይመለከቱት የነበሩት ግብጽ እና ሱዳን በሙሌቱ ደስተኛ አልነበሩም፡፡ እንዳይፈጸም ለማድረግም የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከግድቡ ጋር የተያያዙ ተናጠል እርምጃዎቿን እንድታቆም ከመጠየቅም ባሻገር አፍሪካ ህብረት መር የሆነው የድርድር ሂደት እንዲጓተትና እስከ ጸጥታው ምክር ቤት ጭምር እንዲደርስ በማድረግ ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ እንዲሆን ጥረዋል፡፡
አሜሪካን ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት የድርድር ሂደቱ አካል እንዲሆኑ ደጋግመው ሲጠይቁም ነበር፤ ምንም እንኳ ጉዳዩ አፍሪካዊ እንደሆነና አፍሪካዊ መፍትሔ ሊበጅለት እንጂ ሌሎችን ሊያሳትፍ እንደማይገባ በማሳሰብ ኢትዮጵያ ጥያቄውን ሳትቀበል ብትቀርም፡፡
ምርጫ
ብዙ ሲያነጋግሩ እና ሲያወዛግቡ ከነበሩ አንኳር ሃገራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከ2012 ዓ/ም ጀምሮ ሲራዘም የነበረው 6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ ነው፡፡
ምርጫው ከህወሓት ጋር ጭምር ከነበሩ ጉልህ ልዩነቶች መካከል እንደ አንድ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡
የህዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤት አባላት ይመረጡበት የነበረው ምርጫ በ2012 ዓ/ም የበጋ ወራት ላይ እንደሚካሄድ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ስራዎች በወቅቱ ባለመጠናቀቃቸውና በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ነሀሴ 23 ቀን 2012ዓ.ም እንዲካሄድ እቅድ ተይዞለት ነበር፡፡
ሆኖም በዚህም ጊዜ ማካሄድ እንደማይችል ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማስታወቁ ህገመንግስታዊ ትርጉም ተጠይቆበት ወረርሽኙ የህዝብ ጤና ስጋት አለመሆኑን ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ ከ9 ወር እስከ አንድ አመት ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መወሰኑን ተከትሎ 32 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ድምጽ ሰጥተውበታል የተባለለት 6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ ባሳለፍነው ዓመት ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ/ም መካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ በምርጫው ከተሰጡት ድምጾች አብላጫውን በማግኘትና ከምርጫ ከተካሄደባቸው 436 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች 410 ሩን በማሸነፍ መንግስት ለመመስረት በቅቷል፡፡
ብልጽግና በምርጫው ተፎካክረው መቀመጫዎችን ለማግኘት የቻሉትን የተፎካካሪ ተወካዮች በመዋቅሩ አካቶ አዲስ መንግስት መመስረቱ ይታወሳል፡፡
ከትግራይ ክልል ውጭ ባሉ ሶማሌ ክልልን መሰል አካባቢዎች የተካሄደውን ምርጫ ጨምሮ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ምርጫው ከተካሄደ ከወራት በኋላ መካሄዳቸውና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ 11ኛው የፌዴሬሽኑ አካል ሆኖ መዋቀሩም አይዘነጋም፡፡
አዲስ መንግስት መስረታ
ብልጽግና ፓርቲ ምርጫውን ማሸነፉን ካረጋገጠ በኋላ መንግስት የመመስረቱን ኃላፊነት ተወጥቷል፡፡
ምርጫውን ተከትሎ የተመሰረተው 6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የምስረታ ጉባኤውን አካሂዶ አቶ ታገሰ ጫፎን በአፈ ጉባዔነት ሾሞ በብልጽግና አቅራቢነት የዐቢይ አህመድን (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትርነት አጽድቋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ አቅራቢነት አስፈጻሚው የመንግስት አካል በአዲስ እንዲዋቀር ተደርጎ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮችን ጨምሮ የ22 ሚኒስትሮች ሹመት በምክር ቤቱ ጸድቋል፡፡
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) መሪ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር በለጠ ሞላ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዲሁም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ሊቀመንበር ቀጄላ መርዳሳ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል፤ ቃለ መሃላም ፈጽመዋል፡፡
በየደረጃው ባሉ የመንግስት መዋቅሮች ይኸው እንዲሆንም ተደርጓል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዓለ ሲመትም ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የተለያዩ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች እና በርካታ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም አፍሪካውያን መሪዎች እና ሌሎች ተጋባዥ የክብር እንግዶች በተገኙበት እለተ ሰኞ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ/ም በመስቀል አደባባይ ተፈጽሟል፡፡
በቅርቡ ሁሉን አካታች የሆነ ብሄራዊ የምክክር መድረክ ማካሄድ እንደሚጀመር ጠ/ሚ ዐቢይ ተናገሩ
በበዓለ ሲመቱ የሶማሊያ፣ የኬንያ፣ የጅቡቲ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የናይጄሪያ እና ሴኔጋል መሪዎች ተገኝተዋል፡፡ የተለያዩ ሃገራት መሪዎች የደስታ መግለጫ መላካቸውም ይታወሳል፡፡
ዲፕሎማሲያዊ ጫና
ወትሮውኑ በዓባይ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ ባለችው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት በአንዳንድ ኃያል ነን ባይ ሃገራት ጥርስ ውስጥ የገባችው ኢትዮጵያ በጦርነት መካከልም ውስጥ ሆና አቅልን ለማሳጣት ከሚዳዳቸው ሃገራት ጫና ፈጽሞ አላመለጠችም፡፡
“አስከፊ የሰብዓዊ መብቶች በትግራይ እየተፈጸሙ ነው፣ መንግስት ሰብዓዊ እርዳታዎች እንዳይደርሱ እያደረገ ነው፣ በአስቸኳይ ተኩስ ማቆምና መደራደር አለባችሁ” የሚሉ ጥሪዎች ተደጋግመው ይደረጉ ነበር፡፡
ይህን አድራጊዎቹ አሜሪካን ጨምሮ አውሮፓ ህብረትን መሰል ተቋማት ቀጥተኛ ጫናዎችን ለማድረግ የሞከሩበት ጊዜ እንደነበርም ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
አየርላንድን መሰል ሃገራት የሚጠሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ደጋግሞ መሰብሰቡም ይታወሳል፡፡
ም/ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ንግግራቸው ምን አሉ?
ሆኖም የህወሓት ተዋጊዎች ወደ አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ዘልቀው በገቡበት ጊዜ ጭምር መሰል ጥሪዎችን ሲያደርጉ የነበሩት ሃገራቱ “የህወሓትን ድርጊት ለማውገዝም ሆነ ስለሚፈጸሙ ሰብዓዊ ጥቃቶች ለመናገር አልደፈሩም” እንደ መንግስት ገለጻ፡፡
አሜሪካን መሰል ሃገራት በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሰበብ አይን ያወጣ ጫናን ሲያደርጉ መስተዋላቸው ብዙዎችን ሲያስገርም እና ሲያስቆጭ የነበረም ነው፡፡ “ነጩ ጎርፍ” በሚል ንቅናቄ ለነጩ የፕሬዝዳንት ባይደን ቤተ መንግስት የተቃውሞ ደብዳቤዎችን እስከመጻፍ ተደርሷል፡፡
በተለይ በኢትዮጵያ ባደረጓቸው ተከታታይ ጉብኝቶች ከቁንጮ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ጋር የመከሩትን አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማንን የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛው አድርጎ የሾመው የባይደን አስተዳደር የያዘውና የጉዞ እገዳዎችን እስከመጣል ያደረሰው አቋም ልክ አይደለም በሚል ክፉኛ ሲተች ነበር፡፡
ጉዳዩ የውስጥ የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑን በማስታወቅ እርምጃውን ሲኮንን የነበረው መንግስት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነቷ እና ነፃነት በሚነካ ማንኛውም ጉዳይ ላይ ድርድር እንደማይኖር መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡
ህወሓት አሁን ያለንበት ወቅት ከ1983 ጋር ተመሳሳይ አለመሆኑን ሊረዳ ይገባል- አምባሳደር ፌልትማን
ጣልቃ ገብነቶች ምንም ዐይነት ተቀባይነት እንደሌለው ያስታወቀው ብልጽግና ፓርቲ ጫናዎቹ “በቀይ ባህር የነበረንን ተፅእኖ ፈጣሪነት ለመመለስ ተግተን በመስራታችን” የመጡ ናቸው ሲል ማስታወቁም አይዘነጋም፡፡
ምዕራባውያን ህወሓትን ደግፈው የተመረጠውን መንግስት መንቀፋቸውንና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን ሊያቆሙ ይገባል በሚል የ “በቃ” “ኖ ሞር” ተቃውሞዎች አሁንም በመካሄድ ላይ መሆናቸውም ይታወቃል፡፡